ኢያሱ 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለኤፍሬምና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ የተሰጠ ርስት 1 የዮሴፍም ልጆች ድንበራቸው በኢያሪኮ አንጻር በምሥራቅ በኩል ካለው ከዮርዳኖስ አንሥቶ በምድረ በዳውና በተራራማው በኩል ከኢያሪኮ ሎዛ ትባል ወደ ነበረችው ቤቴል ይደርሳል፤ 2 ከቤቴል ሎዛም በከሮንቲ ዳርቻ በኩል ወደ አጣሮት አውራጃ ይደርሳል፤ 3 ወደ ምዕራብም እስከ የፍሌጣውያን ዳርቻ እስከ ታችኛው ቤቶሮን ዳርቻ ድረስ ይወርዳል፤ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። 4 የዮሴፍም ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ርስታቸውን ወረሱ። የኤፍሬም ልጆች ርስት 5 የኤፍሬምም ልጆች ድንበር በየወገኖቻቸው እንደዚህ ነበረ፤ የርስታቸው ድንበር ከአጣሮትና፥ ከኤሮሕ ምሥራቅ ከጋዛራ እስከ ላይኛው ቤቶሮን ድረስ ነበረ፤ 6 ድንበሩም ወደ ምዕራብ ወደ አካስሞን በቴርማ ሰሜን ያልፋል፤ ወደ ምሥራቅም ወደ ቲናስና ሴላስ ይዞራል፥ ከምሥራቅም ወደ ኢያኖክ ያልፋል። 7 ከኢያኖክም ወደ መአኮና፥ ወደ አጣሮትም፥ ወደ መንደሮቻቸውም ያልፋል፤ ወደ ኢያሪኮም ይገባል፥ ወደ ዮርዳኖስም ይወጣል። 8 ድንበሩም ከጣፉ ወደ ባሕር እስከ ኬልቃን ወንዝ ድረስ ያልፋል፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። የኤፍሬም ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። 9 ይኸውም በምናሴ ልጆች ርስት መካከል ለኤፍሬም ልጆች ከተለዩ ከተሞች ጋር፥ ከተሞች ሁሉ ከመንደሮቻቸው ጋር ነው። 10 በጋዜርም የተቀመጡትን ከነዓናውያንን ኤፍሬም አላጠፋቸውም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ከነዓናውያን በኤፍሬም መካከል ተቀምጠዋል፤ ገባርም ሆኑ። |