ኢያሱ 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለይሁዳ ነገድ የተሰጠ ርስት 1 የይሁዳም ነገድ ድንበር በየወገናቸው ከኤዶምያስ ዳርቻ፥ ከጺን ምድረ በዳ ጀምሮ በዐዜብ በኩል እስከ ቃዴስ ድረስ ነው። 2 በደቡብም በኩል ያለው ድንበራቸው እስከ ጨው ባሕር ዳርቻ ወደ ሊባ እስከሚወስደው መንገድ ነበረ። 3 ከዚያም በአቅረቢን ዐቀበት ፊት ይሄዳል፤ ወደ ጺንም ይወጣል፤ በቃዴስ በርኔ ወደ ደቡብ በኩል ይወጣል፤ በአስሮንም በኩል ያልፋል፤ ወደ ሰራዳም ይወጣል፥ ወደ ቃዴስ ምዕራብም ይዞራል። 4 ወደ አጽሞንም ያልፋል፤ በግብፅም ሸለቆ በኩል ይወጣል፤ የድንበሩም መውጫ በባሕሩ አጠገብ ነበረ፤ በደቡብ በኩል ያለው ድንበራቸው ይህ ነው። 5 በምሥራቅም በኩል ያለው ድንበራቸው እስከ ጨው ባሕር እስከ ዮርዳኖስም ነበረ። በሰሜንም በኩል ያለው ድንበር በዮርዳኖስ መጨረሻ እስካለው እስከ ባሕሩ ልሳን ድረስ ነበረ፤ 6 ከዚያም ድንበራቸው ወደ ቤተ ገለዓም ይወጣል፤ በቤትዓረባ በሰሜን በኩል ያልፋል፤ ድንበራቸውም ወደ ሮቤል ልጅ ወደ ሊቶን ቢዮን ይወጣል፤ 7 ድንበሩም በአኮር ሸለቆ አራተኛ ክፍል ላይ ይወጣል፤ በአዱሚን ዐቀበት ፊት ለፊት፥ በደቡብ በኩል ወዳለችው ወደ ጌልገላ ይወርዳል፤ ድንበሩም ወደ ፀሐይ ምንጭ ውኃ ያልፋል፤ መውጫውም በሮጌል ምንጭ አጠገብ ነበረ፤ 8 ድንበሩም በሄኖም ልጅ ሸለቆ አጠገብ ኢየሩሳሌም ወደምትባለው ወደ ኢያቡስ ወደ ደቡብ ወገን ይወጣል፤ ድንበሩም በሰሜን በኩል በራፋይም ሸለቆ ዳር ባለው በሄኖም ሸለቆ ፊት ለፊት በባሕር በኩል ወዳለው ተራራ ራስ ላይ ይወጣል፤ 9 ድንበሩም ከተራራው ራስ ወደ ኔፍቶ ውኃ ምንጭ ይሄዳል፤ ወደ ዔፍሮንም ተራራ ይደርሳል፤ ወደ ኢያሪም ከተማ ወደ በኣላ ይደርሳል። 10 ድንበሩም ከበኣላ በባሕር በኩል ያልፋል፤ ከዚያም በኢያሪም ከተማ ደቡብ በኩልና በኪስሎን ሰሜን በኩል ወደ አሥራቱስ ድንበር ያልፋል፤ በፀሐይ ከተማም ላይ ይወርዳል፤ በሊባም በኩል ያልፋል። 11 ድንበሩም ወደ አቃሮን ደቡብ ይወጣል፤ ወደ ሰሜን ወገን ይመለሳል፤ ድንበሩ ወደ ሰቆት ይወጣል፤ ወደ ደቡብም ያልፋል፤ በሌብና በኩልም ይወጣል፤ የድንበሩም መውጫ በባሕሩ አጠገብ ነበረ። 12 በባሕር በኩል ያለው ድንበራቸውም እስከ ታላቁ ባሕርና እስከ ዳርቻው ድረስ ነበረ። ለይሁዳ ልጆች በየወገናቸው በዙሪያው ያለ ድንበራቸው ይህ ነው። ካሌብ ኬብሮንንና ዳቤርን እንደ ያዘ ( መሳ. 1፥11-15 ) 13 በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ በይሁዳ ልጆች መካከል ድርሻውን ሰጠው፤ ኢያሱም የዔናቅ ዋና ከተማ የሆነችውን የአርቦቅን ከተማ ሰጠው። እርስዋም ኬብሮን ናት። 14 የዮፎኒ ልጅ ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ልጆች ሱሲን፥ ተለሚንና አካሚን ከዚያ አጠፋቸው። 15 ከዚያም ካሌብ በዳቤር ሰዎች ላይ ዘመተ፤ የዳቤርም ስም አስቀድሞ “ሀገረ መጻሕፍት” ነበረ። 16 ካሌብም፥ “ሀገረ መጻሕፍትን ለሚመታ፥ ለሚይዛትም ልጄን አክሳን ሚስት ትሆነው ዘንድ እሰጠዋለሁ” አለ። 17 የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ልጁን አክሳንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። 18 እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ “አባቴን እርሻ ልለምነው” ብላ አማከረችው፤ እርስዋም በአህያዋ ላይ ሆና ጮኸች፤ ካሌብም፥ “ምን ሆንሽ?” አላት። 19 እርስዋም፥ “በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብ በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና አሁን ደግሞ የውኃውን ምንጭ ስጠኝ” አለችው። እርሱም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጭ ሰጣት። የይሁዳ ነገድ ርስት 20 በየወገኖቻቸውም የይሁዳ ልጆች ነገድ ርስት ይህ ነው። 21 በደቡብም በኩል በምድራቸው ዳርቻ እስከ ኤዶምያስ ድንበር ያሉት የይሁዳ ልጆች ነገድ ከተሞች እነዚህ ነበሩ፤ ቤሴሌኤል፥ አራ፥ አሦር፤ 22 ኤቃም፥ ሬግማ፥ አሩሔል፤ 23 ቃዴስ፥ አሶርዮስም፤ ሚናን፤ 24 በልማንና መንደሮቻቸውም፤ 25 የአሴሮም ከተሞች እርስዋም አሶር ናት። 26 ሲን፥ ሰላማዓ፥ ሞላዳ፤ 27 ሴሪ፥ ቤፋላድ፤ 28 ኮላሴዎል፥ ቤርሳቤሕና መንደሮቻቸው። 29 ባላ፥ ባቆብና አሶም፤ 30 ኤለቦሂዳድ፥ ቤቴልና ኤርማም፤ 31 ሴቄላቅ፥ ማኬሪምር፥ ሴቱናቅ፤ 32 ላቦስ ሳሌ፥ ኤርሞትም ሃያ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 33 በቆላው፥ አስጣል፥ ሳራዓ፥ አሳ፤ 34 ራሜ፥ ጣኖ፥ ኢዱቶት፥ መሐንስ፤ 35 ኤርሙት፥ ኤዶላም፥ ሜምብራ፥ ሰአክ፥ አዚቃ፤ 36 ሴቃርም፥ ጋዴርና ሰፈሮችዋ፥ ዐሥራ አራት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 37 ሴና፥ አዳሶን፥ ማጋዳልጋድ፤ 38 አዶላል፥ መሴፋ፥ ይቃሩል፥ ለኪስ፤ 39 በሴዶት ይዴሃ፥ ደልያም፤ 40 ኮብራ፥ ማኬስ፥ መሐኮስም፤ 41 ጌዶር፥ በጋድያል፥ ኖማን፥ መቄዶም፥ ዐሥራ ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 42 ሌምና፥ ኤተቅ፥ አኖክ፥ 43 ኢድና ናሲብም፤ 44 ኤላም፥ አቁዛም፥ ኬዜብ ቴርሳ፥ ኤሎምም፥ ዐሥር ከተሞችና መንደሮቻቸው። 45 አቃሮን ከመንደሮችዋና ከመሰማሪያዎችዋ ጋር። 46 ከአቃሮንና ከጌምና ጀምሮ በአሴዶት አቅራቢያ ያሉ ሁሉና መንደሮቻቸው፤ 47 አሴያዶት መንደሮችዋና መሰማሪያዎችዋም፥ ጋዛም መንደሮችዋና መሰማሪያዎችዋም እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ፥ ታላቁ ባሕርም ወሰኑ ነው። 48 የሳምር ተራራዎች ፥ ኢዩቴር፥ ሦካ፤ 49 ሬና፥ የመጽሐፍ ሀገር የሆነች ዳቤር፤ 50 አኖን፥ ሴቄማ፥ ኤሳማም፤ 51 ጎሶም ከሉም፥ ከናም፥ ዐሥራ አንድ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 52 ኤሬም፥ ሬምና፥ ሶማ፤ 53 ኢያማይን፥ ቤታቁም፥ ፋቁሕ፤ 54 ኤውማ፥ የአርቦቅ ከተማ እርስዋም ኬብሮን ናት፥ ሶሬት፥ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 55 ማሖር፥ ኬርሜል፥ አዚብ፥ ኢጣን፤ 56 ኢያሬዬል፥ ኢያሪቅም፥ ዘቃይንም፤ 57 ጋባ፥ ተምና፥ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 58 አሌዋ፥ ቤተሱር፥ ጌዶር፤ 59 ማዕራት፥ ቤትአኖት፥ ኤልትቆን፥ ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 60 ቴቆ፥ ኤፍራታ፥ ይኽችውም ቤተ ልሔም ናት፤ ፋጎርም፥ ኤጣንም፥ ቁሎን፥ ጠጦንም፥ ሶብሄም፥ ቃሬም፥ ጌሌም፥ ኤቴር፥ መነኮም፥ ዐሥራ አንድ ከተሞችና መንደሮቻቸው፥ ቅርያትበኣል፥ ይኽችውም የኢያርም ከተማ ናት፤ ሶቤታ፥ ሁለቱ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 61 ባዳርጊስ፥ ተራብዐምም፥ ኤኖን፤ ሴኬዎዛን፥ 62 ናፍላዛንና ከተሞቻቸው፥ ሳዶን፥ አቃዴስ፥ ሰባት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 63 በኢየሩሳሌም የተቀመጡትን ኢያቡሴዎናውያንን ግን የይሁዳ ልጆች ሊያሳድዱአቸው አልተቻላቸውም፤ ኢያቡሴዎናውያንም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ልጆች መካከል በኢየሩሳሌም ውስጥ ተቀምጠዋል። |