ዮናስ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር ምሕረትና የዮናስ ብስጭት 1 ዮናስም ፈጽሞ አዘነ፤ ተከዘም። 2 ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ በሀገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የምትመለስ አምላክ እንደ ሆንህ ዐውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር። 3 አሁንም አቤቱ! ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ! ነፍሴን ከእኔ ውሰድ።” 4 እግዚአብሔርም ዮናስን፥ “ፈጽመህ ታዝናለህን?” አለው። 5 ዮናስም ከከተማዪቱ ወጣ፤ በከተማዪቱም ፊት ለፊት ተቀመጠ፤ በከተማዪቱም የሚሆነውን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ። 6 እግዚአብሔር አምላክም ቅልን አዘዘ፤ ከጭንቀቱም ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ራስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት፤ ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው። 7 በነጋው ግን ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘዘ፤ እርስዋም ቅሊቱን መታቻት፤ ደረቀችም። 8 ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ነፋስን አዘዘ፤ ዮናስንም እስኪዝል ድረስ ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለራሱም ተስፋ ቈርጦ፥ “ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” አለ። 9 እግዚአብሔርም ዮናስን፥ “በውኑ ስለዚች ቅል ታዝናለህን?” አለው። እርሱም፥ “እስክሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ” አለ። 10 እግዚአብሔርም፥ “አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት፥ ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። 11 እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” አለው። |