ኢዩኤል 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የአንበጣ መንጋ መዓት 1 ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዮኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 እናንተ ሽማግሌዎች! ይህን ስሙ፤ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ። ይህ በዘመናችሁ ወይስ በአባቶቻችሁ ዘመን ሆኖ ነበርን? 3 ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፤ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፥ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ። 4 ከተምች የቀረውን አንበጣ በላው፤ ከአንበጣም የቀረውን ደጎብያ በላው፤ ከደጎብያም የቀረውን ኩብኩባ በላው። 5 እናንተ ሰካራሞች፥ ንቁ፤ ለመስከርም ወይንን የምትጠጡ እናንተ ሁላችሁ! ተድላና ደስታ ከአፋችሁ ጠፍትዋልና አልቅሱ፤ እዘኑም። 6 ቍጥርም የሌለው ብርቱ ሕዝብ በምድሬ ላይ ወጥቶአልና፤ ጥርሳቸው እንደ አንበሳ ጥርስ፥ ክንዳቸውም እንደ አንበሳ ደቦል ክንድ ነው። 7 ወይኔን ባዶ ምድር አደረገው፤ በለሴንም ሰበረው፤ ተመለከተውም፥ ጣለውም፤ ቅርንጫፎቹም ነጡ። 8 ስለ ልጅነት ባልዋ ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ ድንግል አልቅሺ። 9 መሥዋዕቱና የመጠጡ ቍርባን ከእግዚአብሔር ቤት ተወግዶአል፤ በእግዚአብሔርም መሠውያ የምታገለግሉ ካህናቱ፥ አልቅሱ። 10 እርሻው ምድረ በዳ ሆኖአል፤ ምድሪቱም ታልቅስ፤ እህሉ ጠፍቶአልና፥ ወይኑም ደርቆአልና፥ ዘይቱም ጐድሎአልና። 11 መከሩ ከእርሻቸው ጠፍቶአልና ገበሬዎች ስለ ስንዴውና ስለ ገብሱ ዐፈሩ፤ የወይን አትክልተኞችም ስለ ወይኑ አለቀሱ። 12 ወይኑ ደርቆአል፤ በለሱም ጠፍቶአል፤ ሮማኑና ተምሩ፥ እንኮዩም፥ የምድርም ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤ ደስታም ከሰው ልጆች ዘንድ ርቆአል። 13 መሥዋዕቱና የመጠጡ ቍርባን ከአምላካችሁ ቤት ቀርቶአልና እናንተ ካህናት! ማቅ ታጥቃችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የመሠውያ አገልጋዮች! ዋይ በሉ፤ እናንተም የእግዚአብሔር አገልጋዮች ኑና በማቅ ላይ ተኙ። 14 ጾምን ቀድሱ፤ ምህላንም ዐውጁ፤ ሽማግሌዎቹንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም በአንድነት ጩኹ። 15 የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና ለቀኑ ወዮ! ወዮ! እርሱም በጥፋት ላይ እንደ ጥፋት ይመጣል። 16 ከዐይኖቻችሁ ፊት ምግብ፥ ከአምላካችሁም ቤት ደስታና ሐሤት ጠፍቶአል። 17 ጊደሮች ከምሳጋቸው ጠፉ፤ ጎተራዎች ባዶ ሆኑ፤ ዐውድማዎቹም ፈራረሱ፤ እህሉ ደርቆአልና። 18 እንግዲህ ለራሳችን ምን እንሰብስብ? የእንስሳት ጠባቂዎች አለቀሱ፤ ማሰማሪያ የላቸውምና፥ የበጎች መንጋዎችም ጠፍተዋልና። 19 አቤቱ! እሳት የምድረ በዳውን ውበት አጥፍቶአልና፥ ነበልባሉም የዱሩን ዛፍ ሁሉ አቃጥሎአልና ወደ አንተ እጮኻለሁ። 20 ፈሳሹ ውኃ ደርቆአልና፥ እሳቱም የምድረ በዳውን ውበት በልቶአልና የምድር አራዊት ወደ አንተ አንጋጠጡ። |