ኢዮብ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢዮብ መልስ 1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦ 2 “በእውነት እንዲህ እንደ ሆነ ዐወቅሁ፤ ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን እንዴት ይችላል? 3 ከእርሱ ጋር ይከራከር ዘንድ ቢወድድ፥ ከሺህ ነገር አንዱን መመለስ አይችልም። 4 በልቡ ጠቢብ ነው፥ ኀይለኛም፥ ታላቅም ነው፤ ክፉስ ሆኖ በፊቱ የቆመ ማን ነው? 5 ተራሮችን ይነቅላል፤ አያውቁትምም፤ በቍጣውም ይገለብጣቸዋል። 6 ምድርን ከሰማይ በታች ከመሠረቷ ያናውጣታል፥ ምሰሶዎችዋም ይንቀጠቀጣሉ። 7 ፀሐይን ያዝዛታል፥ አትወጣምም፤ ከዋክብትንም ያትማል። 8 ሰማያትን ብቻውን ይዘረጋል፥ በምድር ላይ እንደሚሄድ በማዕበል ላይ ይሄዳል። 9 ድብ የሚባለውን ኮከብና ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ፥ የአጥቢያ ከዋክብትንም፥ በአዜብም በኩል ያሉትን የከዋክብት ማደሪያዎች ፈጥሮአል። 10 ታላቁንና የማይመረመረውን ነገር፥ እንዲሁም የከበረውንና እጅግ መልካም የሆነውን የማይቈጠረውንም ተአምራት አደረገ። 11 እነሆ፥ ቢመጣብኝ አላየውም፤ ቢያልፍብኝም አላውቀውም። 12 እርሱ ቢያርቅ የሚመልስ ማን ነው? እርሱንስ፦ ምን ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? 13 እግዚአብሔር እኔን ከመቅጣት አልተመለሰም፥ ከእርሱም የተነሣ ከሰማይ በታች ያሉ አናብርት ይዋረዳሉ። 14 ቃሌን እንዴት ይሰማኛል? እንዴትስ ይተረጕመዋል? 15 በጽድቅ ብጠራው፥ ባይሰማኝም፥ የእርሱን ፍርድ እለምናለሁ። 16 ብጠራው፥ እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ እንደ ሰማኝ አላምንም ነበር። 17 “በዐውሎ ነፋስ ይቀጠቅጠኛል፤ ያለ ምክንያት ብዙ ጊዜ ያቈስለኛል። 18 እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፤ ነገር ግን መራራ ነገርን አጥግቦኛል። 19 እርሱ በኀይል ይይዛልና፤ ፍርዱን ማን ይቃወማል? 20 ጻድቅ ብሆን አፌ ይወቅሰኛል፤ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል። 21 ንጹሕ ነኝ፤ ራሴንም አላውቅም፤ ነገር ግን ሕይወቴ ጠፋች። 22 “ስለዚህ እንዲህ እላለሁ፦ ታላቁና ኀያሉ መቅሠፍትን ይልካል። 23 የኃጥኣን ሞታቸው ክፉ ነውና፥ በጻድቃን ይስቃሉ። 24 በኃጥኣን እጅ ተሰጥተዋልና፤ የምድር ፈራጆችን ፊት ይሸፍናል፤ እርሱ ካልሆነ ማን ነው? 25 ሕይወቴ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፤ ይሸሻል፥ መልካምንም አያይም። 26 የመርከብ መንገድ ፍለጋ፥ ወይም የሚበርና የሚበላውን የሚፈልግ የንስር ፍለጋ እንደማይታወቅ ሕይወቴ እንዲሁ ሆነ። 27 እኔ ብናገር የሚጠቅመኝ የለም፤ ፊቴም በጩኸት ወደቀ፤ 28 ሰውነቶቼ ሁሉ ተነዋወጡ፤ እንግዲህ ንጹሕ አድርገህ እንደማትተወኝ አውቃለሁ፥ 29 “ኃጢኣተኛ ሰው ከሆንሁ፤ ስለ ምን አልሞትሁም? 30 ብታጠብ፥ እንደ በረዶም ብነጻ፥ እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥ 31 በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፤ ልብሴም ይጸየፈኛል። 32 የሚከራከረኝ ሰው ቢሆን ኖሮ፥ ወደ አደባባይ በአንድነት በሄድን ነበር! 33 ማዕከላዊ ዳኛ ቢኖር፥ በሁለታችንም መካከል የሚሰማ ቢገኝ ኖሮ፥ 34 በትሩ ከእኔ ላይ በራቀ ነበር፤ ግርማውም ባላስፈራኝ ነበር። 35 እናገርም ነበር፤ አልፈራምም ነበር፤ የማውቀውም ነገር የለም። |