ኤርምያስ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢየሩሳሌም በደል 1 “በኢየሩሳሌም መንገዶች ሩጡ፤ ተመልከቱም፤ ዕወቁም፤ በአደባባይዋም ፈልጉ፤ ፍርድን የሚያደርገውን እውነትንም የሚሻውን ሰው ታገኙ እንደ ሆነ ይቅር እላቸዋለሁ ይላል እግዚአብሔር። 2 እነርሱም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ቢሉ የሚምሉት በሐሰት ነው።” 3 አቤቱ! ዐይኖችህ ለሃይማኖት አይደሉምን? አንተ ቀሥፈሃቸዋል፤ ነገር ግን አላዘኑም፤ ቀጥቅጠሃቸውማል፤ ነገር ግን ተግሣጽን እንቢ አሉ፤ ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠንክረዋል፤ ይመለሱም ዘንድ እንቢ አሉ። 4 እኔም እንዲህ አልሁ፥ “የእግዚአብሔርን መንገድና የአምላካቸውን ፍርድ አላወቁምና እነዚህ በእውነት ድሆችና ደካሞች ናቸው፤ 5 ወደ ታላላቆቹ እሄዳለሁ እናገራቸውማለሁ፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን መንገድና የአምላካቸውን ፍርድ ያውቃሉና።” እነዚህ ግን ቀንበሩን በአንድነት ሰብረዋል፤ እስራቱንም ቈርጠዋል። 6 ስለዚህ ኀጢአታቸው በዝቶአልና፥ የዐመፃቸውም ብዛት ጸንቶአልና አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰብራቸዋል፤ የበረሃም ተኵላ ያጠፋቸዋል፥ ነብርም በከተሞቻቸው ላይ ይተጋል፤ ከዚያም የሚወጣ ሁሉ ይነጠቃል። 7 “ከእነዚህ ነገሮች በየትኛው ይቅር እልሻለሁ? ልጆችሽ ትተውኛል፤ አማልክትም ባልሆኑ ምለዋል፤ አጠገብኋቸውም፤ እነርሱ ግን አመነዘሩ፤ በአመንዝራዎቹም ቤት ዐደሩ። 8 እንደ አለሌ ፈረሶች ሆኑ፤ እያንዳንዳቸውም የባልጀሮቻቸውን ሚስቶች አረከሱ። 9 በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን? 10 “ወደ ቅጥርዋ ወጥታችሁ አፍርሱ፤ ነገር ግን ፈጽማችሁ አታጥፉ፤ የእግዚአብሔር ናቸውና መጠጊያዎችዋን አትርፉ። 11 የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት በእኔ ላይ እጅግ ወንጅለዋል” ይላል እግዚአብሔር። 12 የይሁዳም ወገኖች በእግዚአብሔር ዋሹ፤ እንዲህም አሉ፥ “እንደዚህ አይደለም፤ ክፉ ነገርም አይመጣብንም ሰይፍንና ራብንም አናይም፤ 13 ነቢያቶቻችን ነፋስ ናቸው፤ የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ የለም፤ እንዲህም ይደረግባቸዋል።” እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደተዋቸው 14 ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እንደዚህ ያለ ቃል ተናግራችኋልና እነሆ በአፍህ ውስጥ ቃሌን እሳት፥ ይህንም ሕዝብ እንጨት አደርጋለሁ፤ ትበላቸውማለች። 15 የእስራኤል ቤት ሆይ! እነሆ ሕዝብን ከሩቅ አመጣባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ኀያል ጥንታዊ ሕዝብ ነው፤ ቋንቋቸውንም የማታውቀው፥ የሚናገሩትንም የማታስተውለው ሕዝብ ነው። 16 ከንፈራቸውም እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ ሁሉም ኀያላን ናቸው። 17 መከርህንና እንጀራህን ይበላሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህንም ይበሉአቸዋል፤ በጎችህንና ላሞችህንም ይበላሉ፤ ወይንህንና በለስህንም፥ ዘይትህንም ይበላሉ፤ የምትታመናቸውን የተመሸጉ ከተሞችህንም በሰይፍ ያጠፋሉ።” 18 ነገር ግን “በዚያ ዘመን ይላል እግዚአብሔር፤ ፈጽሜ አላጠፋችሁም።” 19 እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ፥ “አምላካችን እግዚአብሔር ይህን ነገር ሁሉ ስለ ምን አደረገብን?” ብትሉ፥ አንተ፥ “እንደ ተዋችሁኝ፥ በሀገራችሁም ሌሎችን አማልክት እንዳመለካችሁ፥ እንዲሁ ለእናንተ ባልሆነ ሀገር ለሌሎች ሰዎች ትገዛላችሁ” ትላቸዋለህ። እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዳስጠነቀቀ 20 ይህንም በያዕቆብ ቤት አውሩ፤ በይሁዳም አሰሙ፦ 21 እናንተ ሰነፎች ልበ ቢሶች፥ ዐይን እያላችሁ የማታዩ፥ ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ ሕዝብ ሆይ! ይህን ስሙ። 22 በውኑ እኔን አትፈሩምን? ከፊቴስ አትደነግጡምን? ይላል እግዚአብሔር፤ እንዳያልፍ አሸዋን በዘለዓለም ትእዛዝ ለባሕር ዳርቻ አድርጌአለሁ፤ ሞገዱም ቢትረፈረፍና ቢጮኽ ከእርሱ አያልፍም። 23 ለዚህም ሕዝብ የማይሰማና የዐመፀ ልብ አላቸው፤ ተመልሰውም ሄደዋል። 24 በልባቸውም፦ የመከሩንና የበልጉን ዝናብ በጊዜ የሚሰጠውን፥ ለመከርም የተመደቡትን ወራት የሚጠብቅልንን አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ አላሉም። 25 በደላችሁም እነዚህን አስቀርታለች፤ ኀጢአታችሁም መልካምን ነገር ከእናንተ አርቃለች። 26 በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፤ ሰዎችንም ይዘው ይገድሉ ዘንድ ወጥመድን ይዘረጋሉ። 27 ቀፎ ወፎችን እንደሚሞላ፥ እንዲሁ ቤታቸው ሽንገላን ሞልታለች፤ በዚህም ከብረዋል ባለጸጎችም ሆነዋል። 28 ፍርድን አጣመሙ ለድሃአደጎች ፍርድን አልፈረዱም፤ ለመበለቷም አልተሟገቱም። 29 በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን? 30 የምትሰቀጥጥና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች፤ 31 ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእጃቸው ያጨበጭባሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ? |