ኢሳይያስ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለሚመጣው ንጉሥ 1 የዚህም ጊዜው እስከሚደርስ የተቸገረው ሁሉ አያመልጥም፤ በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፤ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። 2 በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው። 3 ብዙ ሕዝብን በደስታ አወረድህ፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ምርኮንም እንደሚካፈሉ በፊትህ ደስ ይላቸዋል። 4 በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ በላያቸው የነበረው ቀንበር ተነሥቶአልና፥ በጫንቃቸው የነበረውንም፥ የአስጨናቂዎችንም በትር መልሶአልና። 5 በደም የተለወሰ ልብስ በእሳት ከሚቃጠል በቀር ለምንም አይጠቅምም። 6 ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፤ 7 ለአለቆች ሰላምን ለእርሱም ሕይወትን አመጣለሁና፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ ግዛቱ ታላቅ ይሆናል፤ በዳዊት ዙፋን መንግሥቱ ትጸናለች፤ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንዐት ይህን ያደርጋል። 8 ጌታ በያዕቆብ ላይ ሞትን ላከ፤ በእስራኤልም ላይ ወደቀ። 9 የኤፍሬም ሕዝብ ሁሉና በሰማርያ የሚኖሩ ያውቃሉ፤ በትዕቢትና በልብ ኵራትም እንዲህ ይላሉ፦ 10 “ጡቡ ወደቀ፤ ነገር ግን ኑ፥ ድንጋይ እንውቀር፤ ሾላው ነቀዘ፤ ነገር ግን ፅድን እንቍረጥ፤ ለራሳችንም ግንብን እንሥራ።” 11 ስለዚህ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይ እርሱን በመቃወም የሚነሡትን ይበትናቸዋል። 12 ጠላቶቹን ሶርያውያንንም ከምሥራቅ፥ አረማውያንንም ከምዕራብ ያንቀሳቅስበታል፤ እስራኤልንም በተከፈተ አፍ ይበሉታል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 13 ሕዝቡ ግን እስከተቀሠፉ ድረስ አልተመለሱም፤ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን አልፈለጉም። 14 ስለዚህ እግዚአብሔር ራስንና ጅራትን፥ ታላቁንና ታናሹን በአንድ ቀን ከእስራኤል ይቈርጣል። 15 ሽማግሌውና ለፊት የሚያደላው እርሱ ራስ ነው፤ ዐመፅንም የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው። 16 ይህን ሕዝብ የሚያመሰግኑ ያስቱአቸዋል፤ ይበሉአቸውም ዘንድ ያስቱአቸዋል፤ 17 ሰው ሁሉ ክፉና በደለኛ ነውና፥ አፍም ሁሉ ዐመፅን ይናገራልና፥ ስለዚህ ጌታ በጐልማሶቻቸው ደስ አይለውም፤ ለሙት ልጆቻቸውና ለመበለቶቻቸውም አይራራም። በዚህ ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 18 ኀጢአት እንደ እሳት ይነድዳል፤ እሳት እንደ በላችው ደረቅ ሣር ይቃጠላል፤ እንደ ዱር ሣርም ይቃጠላል፤ በተራራዎች ዙሪያ ያለው ሁሉ አብሮ ይቃጠላል። 19 በእግዚአብሔር ቍጣ ምድር ሁሉ ትቃጠላለች፤ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም። 20 ነገር ግን ሰው ወደ ቀኙ ይመለሳል፤ ይራባልና፤ በግራም በኩል ይበላል፤ አይጠግብምም፤ 21 እያንዳንዱም የክንዱን ሥጋ ይበላል፤ ምናሴ ኤፍሬምን፥ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ እነርሱ በአንድነት የይሁዳ ጠላቶች ይሆናሉና። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። |