ኢሳይያስ 61 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የድኅነት መልካም ዜና 1 የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን፥ ለታሰሩትም መፈታትን፥ ለዕውራንም ማየትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። 2 የተወደደችውን የእግዚአብሔርንም ዓመት የተመረጠች ብዬ እጠራት ዘንድ፥ አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ፥ 3 እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድም ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል። 4 ከጥንት ጀምሮ የፈረሱትን ይሠራሉ፤ ከቀድሞ ጀምሮ የፈረሱትንም ያቆማሉ፤ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደ ገና ያድሳሉ። 5 መጻተኞችም መጥተው በጎቻችሁን ይጠብቃሉ፥ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። 6 እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፤ የአምላካችንም አገልጋዮች ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፤ በሀብታቸውም ትመካላችሁ። 7 ሌላ ምድርን ይወርሳሉ፤ በራሳቸውም ዘለዓለማዊ ደስታ አላቸው። 8 እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን የምወድድ፥ ስርቆትንና ቅሚያን የምጠላ ነኝ፤ እንደ ሥራቸውም ለጻድቃን እከፍላቸዋለሁ፤ ከእነርሱም ጋር የዘለዓለምን ቃል ኪዳን አደርጋለሁ። 9 ዘራቸው በአሕዛብ መካከል፥ ልጆቻቸውም በወገኖች መካከል የታወቁ ይሆናሉ፤ ያያቸው ሁሉ እግዚአብሔር የባረካቸው ዘር እንደ ሆኑ ያውቃል፤ 10 በእግዚአብሔርም እጅግ ደስ ይላቸዋል። ነፍሴም በእግዚአብሔር ሐሤት ታደርጋለች። ሽልማትን እንደ ለበሰ ሙሽራ፥ በጌጥ ሽልማቷም እንዳጌጠች ሙሽራ፥ የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፥ የደስታንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና። 11 ምድርም ቡቃያውን እንደምታወጣ፥ ገነትም ዘሩን እንደሚያበቅል፥ እንዲሁ ጌታ እግዚአብሔር ጽድቅንና ደስታን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያበቅላል። |