ኢሳይያስ 55 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር ምሕረት 1 እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ሂዱ፤ ገንዘብም የሌላችሁ ሂዱና ግዙ፤ ብሉ፤ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ጠጡ። 2 ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፤ በረከትንም ብሉ፤ ሰውነታችሁም በበረከት ደስ ይበለው። 3 ስሙኝ፤ ጎዳናዬን ተከተሉ፤ አድምጡኝም፤ ሰውነታችሁም በበረከት ትኖራለች፤ የታመነችዪቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘለዓለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። 4 እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን አደረግሁት። 5 እነሆ፥ የማያውቁህ ሕዝብ ይጠሩሃል፤ የእስራኤል ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ እግዚአብሔር የማያውቁህ ሕዝብ በአንተ ይማጠናሉ። 6 እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ 7 ክፉ ሰው መንገዱን፥ በደለኛም ዐሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ፤ እርሱም ይምረዋል፤ እርሱ ብዙ በደላችሁን ይተውላችኋልና። 8 ዐሳቤ እንደ ዐሳባችሁ፥ መንገዴም እንደ መንገዳችሁ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር። 9 ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ፥ ዐሳቤም ከዐሳባችሁ የራቀ ነው። 10 ብዙ ዝናምና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርን ለሚዘራ፥ እህልንም ለምግብ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ 11 ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ነው፤ የምሻውን እስኪያደርግ ድረስ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም፤ መንገዴንና ትእዛዜን አከናውናለሁ። 12 እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ፤ በሐሤትም ትማራላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በደስታ ሊቀበሏችሁ ይዘላሉ፤ የሜዳም ዛፎች ሁሉ በቅርንጫፎቻቸው ያጨበጭባሉ። 13 በእሾህም ፋንታ ጥድ፥ በኵርንችትም ፋንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ የእግዚአብሔርም ስም ለዘለዓለም በማይጠፋ ምልክት ይመሰገናል። |