ኢሳይያስ 40 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለእስራኤል ሕዝብ የተነገረ ተስፋ 1 አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ 2 ካህናት ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ወደ ልቧ የሚገባ ነገርን ተናገሩ፤ ውርደቷ እንደ ተፈጸመ፥ ኀጢአቷም እንደ ተሰረየ፥ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኀጢአቷ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች አጽናኑአት። 3 የዐዋጅ ነጋሪ ቃል በምድረ በዳ፥ “የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ለአምላካችንም ጎዳና በበረሃ አስተካክሉ። 4 ሸለቆው ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ጠማማውም ይቅና፤ ሰርጓጕጡም ሜዳ ይሁን፤ 5 የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጥ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ የእግዚአብሔርን ትድግና ይይ፤ እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።” 6 “ጩኽ” የሚል ሰው ቃል፤ “ምን ብዬ ልጩኽ?” አልሁ። “ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፤ የሰውም ክብሩ ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነው። 7 የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። 8 ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።” 9 ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤ ለኢየሩሳሌም የምሥራችን የምትነግር ሆይ፥ ድምፅህን በኀይል አንሣ፤ አትፍራ፤ ለይሁዳም ከተሞች፦ እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለህ ንገር። 10 እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር በኀይሉ ይመጣል፤ በክንዱም ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ ነው። 11 መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፤ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል። 12 ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝሩ የለካ፥ ምድርንም ሁሉ ሰብስቦ በእጁ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን፥ ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው? 13 የእግዚአብሔርን ሕሊና ያወቀ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያማከረው ማን ነው? 14 ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? ፍርድንስ ማን አስተማረው? የጥበብንስ መንገድ ማን አሳየው? 15 እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፤ እንደ ሚዛንም ውልብልቢት ተቈጥረዋል፤ እንደ ኢምንትም ናቸው። 16 ሊባኖስ ለማንደጃ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም። 17 አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፤ እንደ ከንቱ ነገርም ይመስላሉ። 18 እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? 19 እንጨት ጠራቢ በሠራው ምስል፥ ወይስ አንጥረኛ መትቶ በሠራው ወርቅ፥ በወርቅም ለብጦ በሠራው ምስል ትመስሉታላችሁን? 20 ጠራቢው የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፤ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል። 21 አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን? 22 እርሱ የምድርን ክበብ ያጸናል፤ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው፥ እንደ ድንኳንም ለመኖሪያ የሚዘረጋቸው፤ 23 አለቆችንም የሚገዛላቸው እንዳይኖር የሚያደርግ ምድርንም እንደ ኢምንት የሚያደርጋት እርሱ ነው። 24 በእርሱም ላይ ዛፉንና ሣሩን፥ የማይቈጠር ሌላውንም ብዙ ፍጥረት የፈጠረ እርሱ ነው። ነፋስም በነፈሰባቸው ጊዜ ይደርቃሉ፤ ዐውሎ ነፋስም እንደ ገለባ ይጠርጋቸዋል። 25 እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ እግዚአብሔር። 26 ዐይናችሁን ወደ ሰማይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ ይህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? ከዋክብትንም በሙሉ የሚቈጥራቸው እርሱ ነው፤ በየጊዜያቸው ያመጣቸዋል፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በክብሩ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም። 27 ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፥ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ አምላኬም ከእኔ ርቋል፤ ፍርዴንም ትትዋል፤ ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? 28 አሁንም አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘለዓለም አምላክ፥ የምድርንም ዳርቻ የፈጠረ አምላክ ነው፤ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ ማስተዋሉም አይመረመርም። 29 ለደካሞች ኀይልን ይሰጣል፤ መከራ የሚቀበሉትንም አያሳዝናቸውም። 30 ብላቴኖች ይራባሉ፤ ጐልማሶች ይታክታሉ፤ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይዝላሉ። 31 እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉና የሚታገሡ ግን ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር ክንፍ ያወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱምም፤ ይሄዳሉ፤ አይራቡምም። |