ኢሳይያስ 31 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንደሚጠብቃት 1 ርዳታ ለመፈለግ ወደ ግብፅ ለሚወርዱ፥ በፈረሶችና በሰረገሎችም ለሚታመኑ ወዮላቸው! ፈረሰኞቹ ብዙዎች ናቸውና፤ በእስራኤልም ቅዱስ አልታመኑምና፤ እግዚአብሔርንም አልፈለጉምና። 2 እርሱ ግን ጠቢብ ነው፤ ክፉንም ነገር በላያቸው ያመጣል፤ ቃሉንም አይመልስም፤ በክፉዎችም ሰዎች ቤት ላይ በከንቱ ተስፋቸውም ላይ ይነሣል። 3 ግብፃውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ እጁን በዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል፤ ተረጂውም ይወድቃል፤ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ። 4 እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛልና፥ “አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ እንደሚያገሣ፥ ድምፁም ተራሮችን እስኪሞላ በእርሱ ላይ እንደሚጮህ፥ እረኞችም ሁሉ ሲጮሁበት ከብዛታቸው የተነሣ እንደማይፈራ፥ ከድምፃቸውም የተነሣ እንደማይደነግጥ፥ እነርሱም ከቍጣው ብዛት የተነሣ ድል እንደሚሆኑና እንደሚደነግጡ፥ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ይዋጋ ዘንድ ይወርዳል። 5 እንደሚበርር ወፍ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፤ ይከልላታልም፤ ይታደጋታል፤ አልፎም ያድናታል። 6 ትበድሉ ዘንድ ጥልቅ ምክርን የምትመክሩ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ። 7 በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው የሠሩአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ። 8 አሦርም ይወድቃል፤ የሚወድቀውም በሰው ሰይፍ አይደለም፤ የምትበላቸውም የሰው ሰይፍ አይደለችም፤ የሚሸሹም ከሰይፍ ፊት አይደለም ጐልማሶቻቸው ግን ይሸነፋሉ። 9 ዓለትም ትውጣቸዋለች ድልም ይሆናሉ የሸሸም ይያዛል። በጽዮን ዘርእ፥ በኢየሩሳሌምም ቤቶች ያሉት ብፁዕ ነው” ይላል እግዚአብሔር። |