ኢሳይያስ 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ እስራኤል መዳን 1 በዚያም ቀን እግዚአብሔር በፈጣኑ እባብ ደራጎን ላይ፥ በክፉውም እባብ ደራጎን ላይ ልዩ፥ ታላቅና ብርቱ ሰይፍን ያመጣል። በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድለዋል። 2 በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት። 3 እኔ የጸናች ከተማ ነኝ፤ አንድዋን ከተማ ይወጋሉ። በከንቱ አጠጣኋት፤ በሌሊት ትጠመዳለች፤ በቀንም ግድግዳዋ ይወድቃል፤ የሚያነሣትም የለም። 4 ስለ ጠቡ በእሳት አቃጥለው ዘንድ ቀርቃሃና ሣርን ማን በሰጠኝ! አሁንም እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ ዛሬ አደረገ፤ እነርሱ ተቃጥለዋልና። 5 በውስጧ የሚኖሩ ይጮሃሉ፤ ከእርሱ ጋር ሰላምን እናድርግ፤ ከእርሱ ጋር ሰላምን እናድርግ። 6 በሚመጣው ዘመን የያዕቆብ ልጆች ሥር ይሰድዳሉ፤ እስራኤልም ያብባል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ። 7 በውኑ የመቱትን እንደ መታ እንዲሁ እርሱን መታውን? ወይስ እነርሱ እንደ ተገደሉበት መገደል እርሱ ተገድሎአልን? 8 በጠብና በንቀት ይሰዳቸዋል፤ በቍጣና በክፉ መንፈስ ትገሥጻቸው ዘንድ ትጀምራለህን? 9 ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፤ ይህም ኀጢአትን የማስወገድ ፍሬ ሁሉ ነው። 10 በዚያም የተሰማራው መንጋ እንደ ተተወ መንጋ ይሆናል፤ ምድሩም ለብዙ ዘመን መሰማሪያ ይሆናል፤ በዚያም መንጋው ይሰማራል፤ ያርፋልም። 11 ዘግይቶ ይደርቃል፤ በውስጡም ልምላሜ ሁሉ አይገኝም፤ ከቲኣሳ የምትመጡ ሴቶች፥ ኑና ለሕዝቤ አልቅሱ፤ የማያስተውል ሕዝብ ነውና፤ ስለዚህ ፈጣሪው አይራራለትም፤ ሠሪውም ምሕረት አያደርግለትም። 12 በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ፈሳሽ ጀምሮ እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ ዐጥር ያጥራል፤ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ። 13 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦርም የጠፉ፥ በግብፅ ምድርም የተሰደዱ ይመጣሉ፤ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ። |