ኢሳይያስ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ እግዚአብሔር ቤት 1 ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ወደ አሞፅ ልጅ ወደ ኢሳይያስ የመጣ ቃል። 2 በኋላ ዘመን እንዲህ ይሆናል፤ የእግዚአብሔር ቤት በተራሮች ራስ ላይ ይታያል፤ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛቡም ሁሉ ወደ እርሱ ይመጣሉ። 3 ሕግ ከጽዮን፥ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ መጥተው፥ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፤ በጎዳናውም እንሄዳለን” ይላሉ። 4 በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፤ ብዙ አሕዛብንም ይዘልፋቸዋል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍን አያነሣም፤ ሰልፍንም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም። 5 አሁንም የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ኑ፤ በእግዚአብሔር ብርሃን እንመላለስ። 6 ሕዝቡን የያዕቆብን ቤት ትቶአልና፤ ምድራቸው እንደ ቀድሞው እንደ ፍልስጥኤማውያን ምድር በሟርት ተሞልቶአልና፤ እንደ ባዕድ ልጆችም ሆነዋልና፤ ብዙ እንግዶች ልጆችም ተወልደውላቸዋልና። 7 ምድራቸውም በብርና በወርቅ ተሞልታለች፤ ለመዛግብቶቻቸውም ቍጥር የለውም፤ ምድራቸውም ደግሞ በፈረሶች ተሞልታለች፤ ለሰረገሎቻቸውም ቍጥር የለውም። 8 ምድራቸውም በእጆቻቸው በሠሩአቸው ጣዖታት ተሞልታለች፤ በጣቶቻቸውም ለሠሩአቸው ይሰግዳሉ። 9 ታናሹም ሰው ዝቅ ብሎአል፤ ታላቁም ሰው ተዋርዶአል፤ ኀጢአታቸውንም ይቅር አልላቸውም። 10 አሁንም ምድርን ያነዋውጣት ዘንድ በተነሣ ጊዜ እግዚአብሔርን ከመፍራትና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻ ግቡ፤ በመሬት ውስጥም ተሸሸጉ። 11 የትዕቢተኞች ሰዎች ዐይኖች ይዋረዳሉ፤ የሰዎችም ኵራት ትወድቃለች፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል። 12 የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን በትዕቢተኛውና በኵራተኛው ሁሉ ላይ ከፍ ባለውም ላይ ይሆናል፤ እነርሱም ይዋረዳሉ፤ 13 ደግሞም በረጅሙ ከፍ ባለውም በሊባኖስ ዝግባ ሁሉ ላይ፥ በባሳንም ዛፍ ሁሉ ላይ፥ 14 በረጅሙም ተራራ ሁሉ ላይ፥ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ 15 በረጅሙም ግንብ ሁሉ ላይ፥ በተመሸገውም ቅጥር ሁሉ ላይ፥ 16 በባሕሩም መርከብ ሁሉ ላይ፥ በተጌጡ ጣዖታትም ምስል ሁሉ ላይ ይሆናል። 17 ሰውም ሁሉ ይዋረዳል፤ የሰውም ኵራት ይወድቃል፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል። 18 በእጅ የተሠሩ ጣዖታትን ሁሉ ይሰውራሉ፤ 19 እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ እግዚአብሔርን ከመፍራትና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ምድር ንቃቃት ውስጥ ያገቡአቸዋል። 20 በዚያም ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጁአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቹን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይጥላል። 21 እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ እግዚአብሔርን ከመፍራትና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ተሰነጠቁ ዓለቶች ውስጥ ያገባሉ። 22 እስትንፋሱ በአፍንጫው ያለበትን ሰው ተዉት፤ እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል? |