ኢሳይያስ 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ኢትዮጵያ የተነገረ 1 በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያላቸው መርከቦች ላሉባት ምድር ወዮላት! 2 መልእክተኞችን በባሕር ላይ፥ ደብዳቤዎችንም በውኃ ላይ ይልካል። ፈጣኖች መልእክተኞች ወደ ረዥምና ወደ ባዕድ፥ ወደ ክፉም ሕዝብ ይሄዳሉና፤ ተስፋ የቈረጡና የተረገጡ ሕዝብ እነማን ናቸው? ዛሬ ግን የምድር ወንዞች ሁሉ፥ ሰዎች እንደሚኖሩባት ሀገር ይኖራሉ። 3 በየሀገራቸው ይቀመጣሉ፤ ከተራሮች ራሶችም እንደ ዓላማ ይይዙታል፤ እንደ መለከት ድምፅም ይሰማል። 4 እግዚአብሔር፥ “እንደ ቀትር ብርሃን፥ በአጨዳም ወራት እንደ ጠል ደመና በማደሪያዬ ጸጥታ ይሆናል” ብሎኛልና። 5 እርሱ ከመከር በፊት አበባ በረገፈ ጊዜ የወይንም ፍሬ ጨርቋ ሲይዝ የወይኑን ቀጫጭን ዘንግ በማጭድ ይቈርጣል፤ ጫፎቹንም ይመለምላል፤ ያስወግድማል። 6 ለሰማይ ወፎችና ለምድር አውሬዎችም በአንድነት ይቀራሉ፤ የሰማይ ወፎችና የምድር አውሬዎችም ሁሉ ይሰበሰቡባቸዋል። 7 በዚያ ዘመን ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር፥ ከተዋረደና ከደከመ ሕዝብ፥ ከዛሬ እስከ ዘለዓለም ታላቅ ከሆነ ወገን፥ ተስፋ ከሚያደርግና ከሚረገጥ፥ በሀገሩ ወንዝ ዳር ከሚኖር ሕዝብ ዘንድ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም በተጠራበት በደብረ ጽዮን እጅ መንሻ ይቀርባል። |