ኢሳይያስ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በይሁዳ የተነገረ ትንቢት 1 በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም፥ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮአልና፥ “ሰማይ ስማ፤ ምድርም አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ፤ አሳደግሁም፤ እነርሱም ዐመፁብኝ። 3 በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጥ ዐወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቁኝም፤ ሕዝቤም አላስተዋሉኝም።” 4 ኀጢአተኛ ወገንና ዐመፅ የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ በደለኞች ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ተዋችሁት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጣችሁት። 5 እንግዲህ በበደል ላይ በደል እየጨመራችሁ ለምን ትቀሠፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕማም፥ ልብም ሁሉ ለኀዘን ሆኖአል። 6 ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፤ አልተጠገነምም፤ በዘይትም አልለዘበም። 7 ምድራችሁ ባድማ ናት፤ ከተሞቻችሁ በእሳት ተቃጠሉ፤ እርሻችሁንም በፊታችሁ ባዕዳን ይበሉታል፤ ጠላትም ያጠፋዋል፤ ባድማም ያደርገዋል። 8 የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፥ እንደ አዝመራ ጠባቂም ጎጆ፥ እንደ ተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች። 9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን፥ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር። 10 እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕግ አድምጡ። 11 “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምንድን ነው?” ይላል እግዚአብሔር፤ “የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤአለሁ፤ የበሬና የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። 12 በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ፥ ይህን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው? እንግዲህ አደባባዬን ደግማችሁ አትረግጡም። 13 መልካሙን የስንዴ ዱቄት ብታመጡ እንኳ ከንቱ ነው፤ ዕጣናችሁ በእኔ ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ መባቻዎቻችሁንና ሰንበቶቻችሁን፥ ታላቋን፥ ቀናችሁን፥ ጾማችሁንና ሥራ መፍታታችሁን አልወድም። 14 መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ አስጸያፊ ሆናችሁብኛል፤ ኀጢአታችሁንም ይቅር አልልም። 15 እጃችሁን ወደ እኔ ብትዘረጉ፥ ዐይኖችን ከእናንተ እመልሳለሁ፤ ምህላንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደምን ተሞልተዋልና። 16 ታጠቡ፤ ንጹሓንም ሁኑ፤ የሰውነታችሁን ክፋት ከዐይኖች ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግንም ተዉ፤ 17 መልካም መሥራትን ተማሩ፤ ፍርድን ፈልጉ፤ የተገፋውን አድኑ፤ ለድሃአደጉ ፍረዱለት፤ ስለ መበለቲቱም ተሙአገቱ።” 18 “ኑና እንዋቀስ” ይላል እግዚአብሔር፤ ኀጢአታችሁ እንደ አለላ ቢሆን እንደ በረዶ አነጻዋለሁ፤ እንደ ደምም ቢቀላ እንደ ባዘቶ አጠራዋለሁ። 19 እሽ ብትሉና ብትሰሙኝ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ 20 እንቢ ብትሉና ባትሰሙኝ ግን ሰይፍ ትበላችኋለች፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። ኀጢአት የሞላባት ከተማ 21 ፍርድ መልቶባት የነበረ የታመነችይቱ የጽዮን ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፤ አሁን ግን ወንበዴዎችና ነፍሰ ገዳዮች አሉባት። 22 ወርቅሽና ብርሽ ዛገ፥ የወይን ጠጅ አሳላፊዎችሽም በወይን ጠጅሽ ላይ ውኃን ይደባልቃሉ። 23 አለቆችሽ ዐመፀኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፤ ፍርድንም ሊያጣምሙ ይፈልጋሉ፤ ለሙት ልጅ አይፈርዱም፤ የመበለቲቱንም አቤቱታ አያዳምጡም። 24 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ለእስራኤል ኀያላን ወዮላቸው! በጠላቶች ላይ ቍጣዬ አይበርድም፤ ጠላቶችንም እበቀላለሁ። 25 እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፤ አግልሻለሁ፤ ዝገትሽንም አነጻለሁ፤ ቆርቆሮሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ፤ ዐመፀኞችን አጠፋለሁ፤ ሕገ ወጦችንም ከአንቺ አስወግዳለሁ፤ ትዕቢተኞችንም አዋርዳለሁ። 26 ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ፥ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያ ጊዜ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ፥ የታመነችም ጽዮን ርእሰ ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ። 27 ምርኮኞችሽ በእውነትና በምጽዋት ይድናሉ። 28 በደለኞችና ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይቀጠቀጣሉ፤ እግዚአብሔርንም የሚተዉት ሁሉ ይጠፋሉ። 29 በወደዱአቸው ጣዖታት ያፍራሉና፥ በፈለጉአቸውም የአድባር ዛፎች ዕፍረት ይይዛቸዋልና፤ 30 ቅጠልዋ እንደ ረገፈ የጠርቤንቶስ ዛፍ፥ ውኃም እንደሌለበት የአትክልት ቦታ ይሆናሉና። 31 ኀይላቸውም እንደ መቃ መስዬ፥ ሥራቸውም እንደ ጠለሸት ይሆናል፤ ኃጥአንና ዐማፅያንም አብረው ይቃጠላሉ፤ እሳቱንም የሚያጠፋላቸው ያጣሉ።” |