ሆሴዕ 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እስራኤል ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ መጠራታቸው 1 ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና ፈጽማ ትጠፋለች፤ በሰይፍም ይወድቃሉ፤ ሕፃኖቻቸውንም ይጥሉአቸዋል፤ እርጉዞቻቸውንም ይሰነጥቋቸዋል። 2 እስራኤል ሆይ! በኀጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ። 3 ከእናንተ ጋር ቃልን ውሰዱ፤ ወደ እግዚአብሔርም ተመለሱ። እንዲህም በሉት፥ “ኀጢአትን ሁሉ አስወግድ፤ በቸርነትም ተቀበለን፤ በወይፈንም ፈንታ የከንፈራችንን ፍሬ ለአንተ እንሰጣለን። 4 አሦር አያድነንም፤ በፈረስም ላይ አንቀመጥም፤ ድሃአደጉም በአንተ ዘንድ ይቅርታን ያገኛልና ከእንግዲህ ወዲህ የእጆቻችንን ሥራ አምላኮቻችን ናችሁ አንላቸውም።” 5 ቍጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ሀገራቸውን አድናለሁ፤ በእውነትም እወድዳቸዋለሁ። 6 ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፤ እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሩን ይሰድዳል። 7 ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፤ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል። 8 ተመልሰውም ከጥላው ሥር ይቀመጣሉ፤ በሕይወትም ይኖራሉ፤ ከእህሉም የተነሣ ይጠግባሉ፤ እንደ ወይንም አረግ ያብባሉ ፤ መታሰቢያውም እንደ ሊባኖስ ወይን ይሆናል። 9 ከእንግዲህ ወዲያ ጣዖት ለኤፍሬም ምንድን ነው? እኔ አደከምሁት፤ አጸናሁትም፤ እኔ እንደ ተወደደ አበባ አፈራዋለሁ፤ ፍሬህም በእኔ ዘንድ ይገኛል። 10 ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ፤ የሚያውቃትም አስተዋይ ማን ነው? የእግዚአብሔር መንገዶች ቀናዎች ናቸው፥ ጻድቃንም ይሄዱባቸዋል፤ ኃጥአን ግን ይወድቁባቸዋል። |