ሆሴዕ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚወድድ 1 እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፤ ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት፤ 2 አብዝች ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ፤ ለበዓሊምም ይሠዉ ነበር፤ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር። 3 እኔም ኤፍሬምን ወደድሁት፤ በክንዴም ተቀበልሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። 4 በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ፊቱን በጥፊ እንደሚመቱት ሰው ሆንሁላቸው፤ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እችለውማለሁ። 5 ኤፍሬም በግብፅ ተቀመጠ፤ አሦርም ንጉሡ ነው፤ መመለስን እንቢ ብሎአልና። 6 ጦር በከተማው ደከመች፤ ከእጁም ይለያታል፤ ከሥራቸውም ፍሬ ይበላሉ። 7 ሕዝቤም ከመኖሪያው ተነሥቶአል፤ እግዚአብሔርም በክብሩ ላይ ተቈጣ፤ ከፍ ከፍም አያደርገውም። 8 እኔም “አምልኮቴን ትተሃል አልሁ፤ ኤፍሬም ሆይ! እንዴት አደርግሃለሁ? እስራኤል ሆይ! እንዴትስ እደግፍሃለሁ? እንዴትስ አደርግሃለሁ? እንደ አዳማ ነውን? ወይስ እንደ ሲባዮ? ልቤ በውስጤ ተናውጣለች፤ ምሕረቴም ተገልጣለች። 9 እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካካልህም ቅዱሱ ነኝና እንግዲህ የቍጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፤ ኤፍሬምንም ያጠፉት ዘንድ አልተውም፤ ወደ ከተማም አልገባም አልሁ። 10 ጌታ እግዚአብሔርን እከተለው ዘንድ እሄዳለሁ፤ እርሱ ያድነናልና፤ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ የውኃ ልጆችም ይደነግጣሉ። 11 እንደ ወፍ ከግብፅ፥ እንደ ርግብም ከአሶር ምድር እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ፤ ወደ ቤታቸውም እመልሳቸዋለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። |