ዕብራውያን 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ቀደመችው ድንኳን 1 ፊተኛይቱም ደግሞ የአገልግሎት ሥርዐትና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ ነበራት። 2 የመጀመሪያዪቱም ድንኳን ተዘጋጅታ ነበርና፥ በእርስዋም ቅድስት በምትባለው ውስጥ መቅረዙና ጠረጴዛው፥ የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበረባት። 3 ከሁለተኛው መጋረጃ በስተኋላ የነበረችውን የውስጠኛዪቱን ድንኳን ግን ቅድስተ ቅዱሳን ይሉአት ነበር። 4 በውስጥዋም የወርቅ ማዕጠንትና ሁለንተናዋን በወርቅ የለበጡአት፥ የኪዳን ታቦት፥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የለመለመችው የአሮን በትር፥ የኪዳኑም ጽላት ነበሩባት። 5 በላይዋም ማስተስረያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ነገር ግን በየመልኩ እናገረው ዘንድ ዛሬ ጊዜው አይደለም። 6 ሥርዐቱ፥ ዝግጅቱም እንዲህ ነበር፤ በመጀመሪያዪቱም ድንኳን በየጊዜው አገልግሎታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ፥ ካህናት ዘወትር ይገቡ ነበር። 7 ወደ ሁለተኛዪቱ ክፍል ግን ሊቀ ካህናቱ ኀጢአታቸውን ለማስተስረይ ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ የሚያቀርበውን ደም ይዞ፥ በየዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻውን ይገባ ነበር። 8 ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። 9 ነገር ግን ለሚያቀርበው ሰው ግዳጅ መፈጸም የማይቻለውን መባና መሥዋዕት ያቀርቡበት የነበረው ለዚህ ዘመን ምሳሌ ሆነ። 10 እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም፥ ስለ ልዩ ልዩ ጥምቀትም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዐቶች ብቻ ናቸው። 11 ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ የሰው እጅ ወደ አልሠራት፥ በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው፥ ከፊተኛዪቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን፥ 12 የዘለዓለም መድኀኒትን ገንዘብ አድርጎ፥ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም። 13 የላምና የፍየል ደም፥ በረከሱትም ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ፥ የሚያነጻና የረከሱትንም ሥጋቸውን የሚቀድሳቸው ከሆነ፥ 14 ነውር የሌለው ሆኖ፥ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እናመልከው ዘንድ ሕሊናችንን ከሞት ሥራ እንዴት ይልቅ ያነጻ ይሆን? 15 ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ተቀብሎ፥ በቀደመው ሥርዐት ስተው የነበሩትን ያድናቸው ዘንድ ወደ ዘለዓለም ርስቱም የጠራቸው ተስፋውን ያገኙ ዘንድ፥ ለአዲሲቱ ኪዳን መካከለኛ ሆነ። 16 ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡ ሰው ሞት ይመጣ ዘንድ ግድ ነው። 17 የሙአች ሰው ኑዛዜ የጸናች ናት፤ ተናዛዡ በሕይወት ባለበት ጊዜ አትጠቅምምና። 18 ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልከበረም። 19 ሙሴ የኦሪትን ትእዛዝ ሁሉ ለመላው ሕዝብ ከነገረ በኋላ፥ የላምና የፍየል ደም ከውኃ ጋር ቀላቅሎ፥ ቀይ የበግ ጠጕርና የስሚዛ ቅጠል ነክሮ መጽሐፈ ኦሪቱንና ሕዝቡን ሁሉ ይረጭ ነበር። 20 “እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው” ይላቸው ነበር። 21 ድንኳኑንና የመገልገያውን ዕቃ ሁሉ በደሙ ይረጭ ነበር። 22 ደግሞም በቀረበው ሁሉ እንዲህ ያደርግ ነበር፥ በኦሪት ሕግ ሁሉ በደም ይነጻ ነበር፤ ደም ሳይረጭ ግን አይሰረይም ነበር። 23 በሰማይ ባለው አምሳል የተሠራው ይህ ሥራ፥ በዚህ ደም የሚነጻ ከሆነ፥ ይህ ሰማያዊ መሥዋዕትስ ከዚህ ይበልጣል። 24 ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ፥ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። 25 ሊቀ ካህናቱ ያደርገው እንደ ነበረ፥ በያመቱም ደም ይዞ ወደ ቅድስት ይገባ እንደ ነበረ ዘወትር ራሱን የሚሠዋ አይደለም። 26 ይህስ ባይሆን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ በሞተ ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ፥ ራሱን በመሠዋት ኀጢአትን ይሽራት ዘንድ አንድ ጊዜ ተገለጠ። 27 ለሰው አንድ ጊዜ ሞት፥ ከዚያም በኋላ ፍርድ እንደሚጠብቀው፥ 28 እንዲሁ ክርስቶስም የብዙዎችን ኀጢአት ያስተሰርይ ዘንድ ራሱን አንድ ጊዜ ሠዋ፤ በኋላ ግን ያድናቸው ዘንድ ተስፋ ለሚያደርጉት ያለ ኀጢአት ይገለጥላቸዋል። |