ዕብራውያን 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጽድቅ ድንኳን 1 ከተናገርነውም ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን። 2 እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር የተተከለች ናት። 3 ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ ይሾማል፤ ለዚህም ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ነገር ይኖረው ዘንድ ይገባል። 4 በምድር ቢሆን ኖሮ፥ ሊቀ ካህናት ባልሆነም ነበር፤ በኦሪት ሕግ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ካህናት በእርስዋ አሉና። 5 እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሲሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ፤ “በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ” ብሎት ነበርና። 6 ዛሬ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የምትበልጠውን አገልግሎት ገንዘብ አደረገ፤ ለታላቂቱ ሥርዐትም መካከለኛ ሆነ፤ የምትበልጠውንም ተስፋ ሠራ። 7 ፊተኛይቱ ያለ ነቀፋ ብትሆን ኖሮ ሁለተኛይቱን ባልፈለገም ነበር። 8 ነገር ግን እነርሱን ነቅፎ እንዲህ አለ፥ “እነሆ፥ ለቤተ እስራኤልና ለቤተ ይሁዳም አዲስ ኪዳን የምሠራበት ዘመን ይመጣል ይላል እግዚአብሔር። 9 እጃቸውን ይዤ ከምድረ ግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ ለአባቶቻቸው እንደ ገባሁት እንደዚያ ያለ ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልኖሩምና፤ እኔም ቸል ብያቸዋለሁና” ይላል እግዚአብሔር። 10 ከእነዚያ ዘመናት በኋላ ለቤተ እስራኤል የምገባው ቃል ይህ ነው፦ ሕጌን በልባቸው አሳድራለሁ፤ በሕሊናቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑኛል ይላል እግዚአብሔር። 11 እንግዲህ አንዱ ሌላውን አያስተምርም፤ ወንድምም ወንድሙን እግዚአብሔርን ዕወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና። 12 ዐመፃቸውን እምራቸዋለሁና ኀጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም።” 13 አዲስ ትእዛዝ በማለቱ የቀደመችቱን አስረጃት፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ለጥፋት የቀረበ ነው። |