ዕብራውያን 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ንስሓ 1 ስለዚህም የክርስቶስን የነገሩን መጀመሪያ ትተን ወደ ፍጻሜው እንሂድ፤ እንግዲህ ደግሞ ሌላ መሠረት እንዳትሹ ዕወቁ፤ ይኸውም ከሞት ሥራ ለመመለስ፥ በእግዚአብሔርም ለማመን፥ 2 ጥምቀትን፥ በአንብሮተ እድ መሾምን፥ የሙታንን ትንሣኤና የዘለዓለም ፍርድን ለመማር ነው። 3 እግዚአብሔርም ቢፈቅድ ይህን ባደረግን ነበር። 4 ነገር ግን አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን፥ ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን፥ ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን፥ 5 መልካሙን የእግዚአብሔርን ቃል፥ የሚመጣውንም የዓለምን ኀይል የቀመሱትን፥ 6 በኋላም የካዱትን እንደ ገና ለንስሓ እነርሱን ማደስ አይቻልም፤ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና፥ ያዋርዱትማልና። 7 ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን ዝናም ከጠጣች፥ ያንጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መላካም ቡቃያ ታበቅላለች፤ ከእግዚአብሔር ዘንድም በረከትን ታገኛለች። 8 እሾህንና ኵርንችትን ብታወጣ ግን የተጣለች ናት፤ ለመርገምም የቀረበች ናት፤ ፍጻሜዋም ለመቃጠል ይሆናል። 9 የተመረጣችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምንም እንኳን እንዲህ ብንላችሁ ሕይወት ወዳለባት ትምህርት እንድትቀርቡ እንታመንባችኋለን። 10 እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስለ አገለገላችሁ፥ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችትሁን ሥራ፥ በስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዐመፀኛ አይደለምና። 11 ነገር ግን ሁላችሁም በዚች ተስፋችሁ እንዲሁ ትጋታችሁን እስከ መጨረሻው ታሳዩ ዘንድ እንወዳለን። 12 ዳተኞች እንዳትሆኑ በሃይማኖትና በትዕግሥት ተስፋቸውን የወረሱትን ሰዎች ምሰሉአቸው። ስለ ተስፋና ስለ መሐላ 13 እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋዉን በሰጠው ጊዜ ይምልበት ዘንድ ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ ባይኖር፥ በራሱ ማለ። 14 እንዲህ ብሎ፦“ መባረክን እባርክሃለሁ፥ ማብዛትንም አበዛሃለሁ።” 15 ከዚህም በኋላ ታግሦ ተስፋዉን አገኘ። 16 ሰው ግን ከእርሱ በሚበልጠው ይምላል፤ የክርክርም መነሻው በመሐላ ይፈጸማል። 17 ስለዚህም እግዚአብሔር ተስፋውን ለሚወርሱ ሰዎች ምክሩን እንደማይለውጥ ሊገልጥ ወደደ፤ እንደማይለውጥም በመሓላ አጸናው። 18 የእግዚአብሔር ቃል ሐሰት ሊሆን አይቻልም፤ በእርሱ ለተማፀን ተጠብቆልን ባለ ተስፋችንም ማመንን ላጸናን ለእኛ ታላቅ ደስታ አለን። 19 ይህችም ተስፋ ነፍሳችን እንዳትነዋወጥ እንደ መልሕቅ የምታጸና ናት፤ 20 እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘለዓለም ሊቀ ካህናት ሆኖ ሐዋርያችን ኢየሱስ ከእኛ በፊት ወደ ገባባት መጋረጃም ውስጥ የምታስገባ ናት። |