ዕብራውያን 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጌታን ስለ መከተል 1 እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ፥ የኀጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ። 2 የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው፤ እርሱ ነውርን ንቆ፥ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። 3 በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኀጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን እስኪ ዐስቡት። 4 ገና አልጸናችሁምና ደማችሁን ለማፍሰስ እስክትደርሱ ኀጢአትን ተጋደሉኣት፥ አሸንፉኣትም፤ ተስፋችሁን የምታገኙባትን ትምህርትም ውደዷት። 5 እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር፥ “ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም። 6 እግዚአብሔር የሚወደውን ይገሥጻልና፥ የሚወደደውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል” ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል። 7 ቅጣታችሁን ታገሡ፤ ልጆቹ እንደ መሆናችሁ ይወዳችኋልና፤ አባቱ የማይቈጣው ልጅ ማን ነው? 8 ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና፥ ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። 9 በሥጋ የወለዱን አባቶቻችን የሚቀጡን፥ እኛም የምንፈራቸው ከሆነ፥ እንግዲያ ይልቁን ለመንፈስ አባታችን ልንታዘዝና ልንገዛ በሕይወትም ልንኖር እንዴት ይገባን ይሆን? 10 እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡናል፤ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። 11 ቅጣት ሁሉ በጊዜው ያሳዝናል እንጂ ደስ አያሰኝም፤ በኋላ ግን ለተቀጡ ሰላምን ያፈራል፤ ጽድቅንም ያሰጣቸዋል። 12 ስለዚህም የላሉትን እጆች፥ የሰለሉትንም ጕልበቶች አቅኑ። 13 አንካሳነታችሁ እንዲድንና እንዳትሰነካከሉ ለእግሮቻችሁ የቀና መንገድን አድርጉ። 14 ከሁሉ ጋር ወደ ሰላም ሩጡ፤ ቅድስናችሁንም አትተዉ፤ ያለ እርሱ ግን እግዚአብሔርን የሚያየው የለም። 15 አስተውሉ፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ የሚያቃልል አይኑር፤ ሕማምን የምታመጣ፥ ብዙዎችንም የምታስታቸውና የምታረክሳቸው መራራ ሥር የምትገኝበትም አይኑር። 16 ለጥቂት መብል ብኵርናውን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ሴሰኛና ርኩስ የሚሆን አይኑር። 17 ከዚያ በኋላ እንኳ በረከትን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባም ተግቶ ምንም ቢፈልጋት ለንስሓ ስፍራ አላገኘምና። 18 ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም፥ ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም፥ 19 ወደ መለከት ድምፅም፥ ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፥ ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ለመኑ። 20 የተነጋገራቸውን ሊሰሙት አልተቻላቸውም ነበርና፥ “እንስሳም ያን ተራራ ቢቀርበው በድንጋይ ይወግሩት” ነበር። 21 የታያቸውም እንዲህ ግሩም ነበር፤ ሙሴም እንኳን፥ “እኔ ፈርቻለሁ፥ ደንግጫለሁም” አለ። 22 እናንተ ግን፥ የሕያው እግዚአብሔር ከተማ ወደምትሆን ወደ ጽዮን ተራራ፥ በሰማያት ወደ አለችው ኢየሩሳሌም፥ ደስ ብሎአቸው ወደሚኖሩ አእላፍ መላእክትም ደርሳችኋል። 23 ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈ ወደ ማኅበረ በኵርም፥ ሁሉን ወደሚገዛም ወደ እግዚአብሔር፥ ወደ ፍጹማን ጻድቃንም ነፍሳት፥ 24 የአዲስ ኪዳንም መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ ተረጨው ደሙ ደርሳችኋል። 25 ለሚናገረው እንቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነርሱ በደብረ ሲና የተገለጠላቸውን እንቢ ስለ አሉት ካልዳኑ፥ ከሰማይ ከመጣው ፊታችንን ብንመልስ እኛማ እንዴታ? 26 ያንጊዜ ቃል ምድርን አናወጣት፤ “አሁንም እኔ ምድርን እንደ ገና አንድ ጊዜ አናውጣታለሁ” ብሎ ተናገረ፤ ምድርን ብቻም አይደለም፤ ሰማይንም ጭምር እንጂ። 27 አንድ ጊዜ ደግሞ ያለውም ፍጡራን ናቸውና፥ የማይናወጠው ይኖር ዘንድ፥ የሚናወጠውን እንደሚያሳልፈው ያሳያል። 28 ስለዚህ የማይናወጥ መንግሥትን ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሀት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ። 29 አምላካችን በእውነት የሚያቃጥል እሳት ነውና። |