ገላትያ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ነገር ግን እላለሁ፤ ወራሹ ሕፃን ሳለ ለሁሉ ጌታ ሲሆን ከአገልጋይ የሚለይ አይደለም። 2 ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ዕድሜ ድረስ በአያት ወይም በሞግዚት እጅ ይጠበቃል። 3 እንዲሁ እኛም ሕፃናት በነበርን ጊዜ፥ ለዚህ ዓለም ስሕተት ተገዝተን ነበር። 4 ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፤ ከሴትም ተወለደ፤ የኦሪትንም ሕግ ፈጸመ። 5 እኛ የልጅነትን ክብር እንድናገኝ በኦሪት የነበሩትን ይዋጅ ዘንድ። 6 ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን እግዚአብሔር አባ አባቴ ብላችሁ የምትጠሩትን የልጁን መንፈስ በልባችሁ አሳደረ። 7 እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፤ ልጆች ከሆናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ። ወደ ጣዖታት ስለ አለመመለስ 8 ነገር ግን ቀድሞ እግዚአብሔርን ባለማወቃችሁ፥ በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑ ተገዝታችሁ ነበር። 9 ዛሬ ግን እግዚአብሔርን ዐወቃችሁት፤ ይልቁንም እርሱ ዐወቃችሁ፤ እንደ ገና ደግሞ ወደዚያ ወደ ደካማው፥ ወደ ድሀው ወደዚህ ዓለም ጣዖት ተመልሳችሁ፥ ትገዙላቸው ዘንድ እንዴት ፈጠራን ትሻላችሁ? 10 ዕለትንና ወርን፥ ጊዜንና ዓመታትን ትጠብቃላችሁ። 11 ስለ እናንተ በከንቱ ደክሜ እንደ ሆነ ብዬ እፈራችኋለሁ። 12 ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሁኛለሁ፤ እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እማልዳችኋለሁ፤ አንዳች አልበደላችሁኝምና። 13 መጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ፥ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበር ታውቃላችሁ። 14 መከራ እቀበል በነበረበት ጊዜ አልሰለቻችሁኝም፤ እንደ እግዚአብሔር መልአክ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስም ተቀበላችሁኝ እንጂ በሰውነቴ አልናቃችሁኝም። 15 አሁንስ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻላችሁስ ዐይናችሁንም እንኳ ቢሆን አውጥታችሁ ትሰጡኝ እንደ ነበረ፥ እኔ ምስክራችሁ ነኝ። 16 እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ባላጋራ ሆንኋችሁን? 17 እነዚያማ ይቀኑባችኋል፤ ነገር ግን በእነርሱ ላይ እንድትቀኑ ሊዘጉአችሁ ይወዳሉ እንጂ ለመልካም አይደለም። 18 መቅናትስ ዘወትር ለመልካም ሥራ ልትቀኑ ይገባል፤ ነገር ግን እኔ ከእናንተ ዘንድ ባለሁበት ጊዜ ብቻ አይደለም። 19 ልጆች፥ እንደ ገና የምጨነቅላችሁ ክርስቶስ በልባችሁ እስኪሣልባችሁ ድረስ ነው። 20 ቃሌን ለውጬ አሁን በእናንተ ዘንድ ልገኝ እሻለሁ፤ ስለ እናንተ የምናገረውን አጣለሁና። 21 በኦሪት ሕግ እንኑር ትላላችሁን? ኦሪትን አትሰሙአትምን? 22 አብርሃም ሁለት ልጆችን አንዱን ከባሪያዪቱ፥ አንዱንም ከእመቤቲቱ እንደ ወለደ ተጽፎአልና። 23 ነገር ግን ከባሪያዪቱ የተወለደው ልደቱ ልዩ ነው፤ በሰው ልማድ ተወለደ፤ ከእመቤቲቱ የተወለደው ግን እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ ተወለደ። 24 ይህም የሁለቱ ሥርዐት ምሳሌ ነው፤ አንዲቱ ከደብረ ሲና ለባርነት ትወልዳለች፤ እርስዋም አጋር ናት። 25 አጋርም በዐረብ ሀገር ያለች ደብረ ሲና ናት፤ ከዛሬዪቱ ኢየሩሳሌም ጋር ትነጻጸራለች፤ ከልጆችዋ ጋርም ትገዛለች። 26 የላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት፤ እርስዋም እናታችን ናት። 27 “የማትወልድ መካን ደስ ይላታል፤ ምጥ የማታውቀውም ደስ ብሎአት እልል ትላለች፤ ባል ካላት ይልቅ የፈቲቱ ልጆች ብዙዎች ናቸውና” ተብሎ ተጽፎአል። 28 ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኛስ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ልጆች ነን። 29 ነገር ግን በሥጋ ልማድ የተወለደው በመንፈሳዊ ግብር የተወለደውን በዚያ ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። 30 ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “የባሪያዪቱ ልጅ ከእመቤቲቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያዪቱን ከልጅዋ ጋር አስወጥተህ ስደዳት” 31 ወንድሞቻችን ሆይ፥ አሁንም እኛ የእመቤቲቱ ነን እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም፤ ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናልና። |