ዘፀአት 40 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ድንኳኑ ተተክሎ ለአገልግሎት መዋሉ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 2 “በመጀመሪያው ወር በፊተኛው ቀን የምስክሩን ድንኳን ትተክላለህ። 3 በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፤ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። 4 ገበታውንም ታገባለህ፤ በሥርዐቱም ታሰናዳዋለህ፤ መቅረዙንም አግብተህ ቀንዲሎቹን ትለኵሳለህ። 5 የወርቁንም ማዕጠንት በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፤ በድንኳኑም ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ትጋርዳለህ። 6 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ በምስክሩ ድንኳን ደጅ ፊት ታኖረዋለህ። 7 የመታጠቢያውን ሰንም በምስክሩ ድንኳንና በመሠዊያው መካከል ታኖረዋለህ፤ በውስጡም ውኃ ትጨምርበታለህ። 8 በዙሪያውም አደባባዩን ትሠራለህ፤ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ትዘረጋለህ። 9 የቅብዐቱንም ዘይት ወስደህ ድንኳኑን፥ በውስጥዋም ያለውን ሁሉ ትቀባለህ፤ እርስዋንም ዕቃዋንም ሁሉ ትቀድሳለህ፤ ቅድስትም ትሆናለች። 10 ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆነውን መሠዊያ፥ ዕቃውንም ሁሉ ትቀባዋለህ፤ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ፤ መሠዊያውም ቅዱሰ ቅዱሳን ይሆናል። 11 የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ቀብተህ ትቀድሳለህ። 12 አሮንንና ልጆቹንም ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ አቅርበህ በውኃ ታጥባቸዋለህ። 13 ለአሮንም የተቀደሰውን ልብስ ታለብሰዋለህ፤ ትቀባዋለህ፤ ትቀድሰውማለህ፤ ካህንም ይሆነኛል። 14 ልጆቹንም ታቀርባቸዋለህ፤ ቀሚሳቸውንም ታለብሳቸዋለህ፤ 15 አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ፤ ካህናትም ይሆኑኛል። ይህም ለልጅ ልጃቸው ለዘለዓለም የክህነት ቅብዐት ይሆንላቸዋል።” 16 ሙሴም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፤ እንዲሁም አደረገ። 17 እንዲህም ሆነ፤ ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት በፊተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ድንኳንዋ ተተከለች። 18 ሙሴም ድንኳንዋን ተከለ፤ እግሮችዋንም አኖረ፤ ሳንቆችዋንም አቆመ፤ መወርወሪያዎችዋንም አደረገባቸው፤ ምሰሶዎችዋንም አቆመ። 19 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው መጋረጃውን በድንኳኑ ላይ ዘረጋው፤ የድንኳኑንም መደረቢያ በላዩ አደረገበት። 20 ሙሴም ጽላቱን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረው፤ መሎጊያዎቹንም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ አደረገ፤ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረው። 21 ታቦቷንም ወደ ድንኳኑ አገባ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ አድርጎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ። 22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ገበታውን በምስክሩ ድንኳን ውስጥ፥ ከመጋረጃው ውጭ በድንኳኑ በመስዕ በኩል አኖረው፤ 23 ኅብስተ ገጹንም በላዩ በእግዚአብሔር ፊት አሰናዳ። 24 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው መቅረዙን በምስክሩ ድንኳን ውስጥ፥ በገበታውም ፊት ለፊት፥ በድንኳኑ በአዜብ በኩል አኖረ፤ 25 ቀንዲሎቹንም በእግዚአብሔር ፊት አበራ። 26 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የወርቁን ማዕጠንት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በመጋረጃው ፊት አኖረ። 27 የአዘጋጀውንም ዕጣን ዐጠነበት። 28 ሙሴም እግዚአብሔር እንደ አዘዘው በድንኳኑ ደጅ ፊት መጋረጃውን ዘረጋ። 29 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያም በምስክሩ ድንኳን ደጅ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በላዩ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን አቀረበ። 30 የመታጠቢያውንም ሰን በምስክሩ ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኖረ፤ ለመታጠቢያም ውኃን ጨመረበት። 31 በእርሱም ሙሴና አሮን፥ ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ታጠቡ፤ 32 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ወደ ምስክሩ ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ወደ መሠዊያውም በቀረቡ ጊዜ ይታጠቡ ነበር። 33 በድንኳኑና በመሠዊያውም ዙሪያ አደባባዩን ሠራ፤ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ዘረጋ። እንዲሁም ሙሴ ሥራውን ፈጸመ። የእግዚአብሔር ክብር ድንኳኑን እንደ ሞላው ( ዘኍ. 9፥15-23 ) 34 ደመናውም የምስክሩን ድንኳን ከደነ፤ ድንኳንዋም የእግዚአብሔርን ክብር ተሞላች። 35 ደመናውም በላዩ ስለነበር ድንኳኑም የእግዚአብሔርን ክብር ስለ ተሞላ ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም። 36 ደመናውም ከድንኳኑ በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በየነገዳቸው ይጓዙ ነበር። 37 ደመናው ካልተነሣ ግን ደመናው እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። 38 ደመና በቀን በድንኳኑ ላይ ነበርና፥ እሳቱም በሚጓዙበት ሁሉ በሌሊት በእስራኤል ሁሉ ፊት በእርስዋ ላይ ነበርና። |