ዘፀአት 34 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እንደ ገና የተሠሩት ጽላቶች ( ዘዳ. 10፥1-5 ) 1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ሁለት የድንጋይ ጽላት እንደ ፊተኞቹ አድርገህ ቅረጽ፤ ወደ እኔም ወደ ተራራ ውጣ፤ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላት የነበሩትን ቃላት እጽፍባቸዋለሁ። 2 ለጥዋትም የተዘጋጀህ ሁን፤ ወደ ሲና ተራራ ወጥተህ በዚያ በተራራው ራስ ላይ በፊቴ ቁም። 3 ከአንተም ጋር ማንም ሰው አይውጣ፤ በተራራውም ሁሉ ማንም አይታይ፤ መንጎችና ከብቶችም በዚያ ተራራ አጠገብ አይሰማሩ። 4 ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጎ ሁለት የድንጋይ ጽላት ቀረጸ፤ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላት በእጁ ወሰደ፤ በነጋውም ማልዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ 5 እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ። 6 ጌታም በፊቱ አለፈ፥ “ስሜም ጌታ እግዚአብሔር፥ መሓሪ፥ ይቅር ባይ፥ ከመዓት የራቀ ምሕረቱ የበዛ ጻድቅ፥ 7 ለብዙ ሺህ ጽድቅን የሚጠብቅ፥ ቸርነትን የሚያደርግ፥ አበሳንና መተላለፍን፥ ኀጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኀጢአት በልጆች፥ እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው” ሲል አወጀ። 8 ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጎነበሰና ለእግዚአብሔር ሰገደ፦ 9 “አቤቱ በፊትህስ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ይህ ሕዝብ አንገተ ደንዳና ነውና ጌታዬ ከእኛ ጋር ይሂድ፤ ጠማማነታችንን፥ ኀጢአታችንንና በደላችንን ይቅር በለን፤ ለአንተም እንሆናለን” አለ። እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን እንደ ገና ማደሱ ( ዘፀ. 23፥14-19 ፤ ዘዳ. 7፥1-5 ፤ 16፥1-17 ) 10 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እነሆ፥ እኔ በሕዝብህ ፊት ሁሉ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በምድር ሁሉ፥ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እንደ እርሱ ያለ ከቶ ያልተደረገውን ታላቅ ተአምራትን አደርግልሃለሁ፤ እኔም የማደርግልህ ነገር ድንቅ ነውና አንተ በመካከሉ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል። 11 በዚህ ቀን የማዝዝህን ነገር ጠብቅ፤ እነሆ፥ እኔ አሞሬዎናዊውን፥ ከነዓናዊውንም፥ ኬጤዎናዊውንም፥ ፌርዜዎናዊውንም፥ ጌርጌሴዎናዊውንም፥ ኤዌዎናዊውንም፥ ኢያቡሴዎናዊውንም ከፊትህ አወጣለሁ። 12 በመካከልህ ወጥመድ እንዳይሆኑብህ አንተ በምትገባበት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ 13 ነገር ግን መሠውያዎቻቸውን ታፈርሳላችሁ፤ ሐውልቶቻቸውንም ትሰብራላችሁ፤ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውን ትቈርጣላችሁ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት ታቃጥላላችሁ፤ 14 ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር ቅንዐት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ። 15 በዚያች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፥ እነርሱ አምላኮቻቸውን ተከትለው በአመነዘሩና በሠዉላቸው ጊዜ እንዳይጠሩህ፥ ከመሥዋዕታቸውም እንዳትበላ፥ 16 ሴቶች ልጆቻቸውምንም ከወንድ ልጆችህ፥ ሴቶች ልጆችህንም ከወንድ ልጆቻቸው ጋር እንዳታጋባ፥ ልጆቻቸውም አምላኮቻቸውን ተከትለው ሲያመነዝሩ ከአምላኮቻቸው በኋላ ሄደው አመንዝረውም ልጆችህን እንዳያስቱ ተጠንቀቅ። 17 ቀልጠው የተሠሩትን አማልክት ለአንተ አታድርግ። 18 “የቂጣውን በዓል ትጠብቀዋለህ። በሚያዝያ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና በታዘዘው ዘመን በሚያዝያ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ ብላ። 19 መጀመሪያ የሚወለድ ተባት ሁሉ የእኔ ነው፤ የላምህም በኵር፥ የበግህም በኵር፥ የበሬህም በኵር ሁሉ የእኔ ነው። 20 የአህያውንም በኵር በበግ ትዋጀዋለህ፤ ባትዋጀው ግን ዋጋውን ትሰጣለህ። የልጆችህንም በኵር ሁሉ ትዋጃለህ። በፊቴም ባዶ እጅህን አትታይ። 21 “ስድስት ቀን ሥራህን ትሠራለህ፤ በሰባተኛውም ቀን ታርፋለህ። በምትዘራበትና በምታጭድበት ዘመን ታርፋለህ። 22 የሰባቱንም ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ፤ እርሱም የስንዴ መከር መጀመሪያ ነው፤ በዓመቱም መካከል የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ። 23 ወንድ ልጅህ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ፊት በዓመት ሦስት ጊዜ ይታይ። 24 አሕዛብን ከፊትህ በአወጣሁ ጊዜ ሀገርህን አሰፋለሁ፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊትም ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም። 25 “የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የፋሲካውም በዓል መሥዋዕት እስከ ነገ አይደር። 26 የመጀመሪያውን የምድርህን ፍሬ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ትወስዳለህ። ጠቦቱን በእናቱ ወተት አትቀቅል።” 27 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “በእነዚህ ቃሎች ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ” አለው። 28 በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም። በጽላቱም ዐሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። የሙሴ ፊት እንደ አበራ 29 እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ ጽላት በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ፊቱ እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። 30 አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እነሆ፥ ፊቱ እንዳንጸባረቀ ሙሴን በአዩ ጊዜ፥ ወደ እርሱ ለመቅረብ ፈሩ። 31 ሙሴም ጠራቸው፤ አሮንም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም ተናገራቸው። 32 ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። 33 ሙሴም ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ። 34 ሙሴም ከእርሱ ጋር ይነጋገር ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በገባ ጊዜ እስኪወጣ ድረስ መሸፈኛውን ከፊቱ ያነሣ ነበር፤ በወጣም ጊዜ ለእስራኤል ልጆች የታዘዘውን ነገር ይነግራቸው ነበር። 35 የእስራኤልም ልጆች የሙሴን ፊት እንዳንጸባረቀ ያዩ ነበር፤ እርሱም ከእርሱ ጋር ሊነጋገር እስኪገባ ድረስ እንደ ገና በፊቱ መሸፈኛ ያደርግ ነበር። |