ኤፌሶን 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ወንድሞቻችን ሆይ፥ ለተጠራሁላት አጠራር በሚገባ ትኖሩ ዘንድ በክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ እማልዳችኋለሁ። 2 በፍጹም የዋህነት ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ እየታገሣችሁ፥ ለወንድሞቻችሁም እሺ እያላችሁ፥ በፍቅር እየተጋችሁና እየተባበራችሁ፥ 3 በአንድ መንፈስና በሰላም ማሰሪያነት እየተጠበቃችሁ፥ 4 ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን፥ አንድ አካልና አንድ መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኋለሁ። 5 ጌታ አንድ ነው፤ ሃይማኖትም አንዲት ናት፤ ጥምቀትም አንዲት ናት። 6 በሁሉ ሙሉ የሚሆን ሁሉም ከእርሱ የተገኘ ከሁሉም በላይ ያለ የሁሉ አባት እግዚአብሔር አንድ ነው። 7 ከእኛ ለእያንዳንዱ በክርስቶስ ስጦታ መጠን ጸጋው ተሰጥቶናል። 8 “ምርኮን ማርከህ ወደ ሰማይ ወጣህ፤ ጸጋህንም ለሰው ልጅ ሰጠህ” ይላልና። 9 ከምድር በታች ካልወረደ መውጣቱ ምንድን ነው? 10 የወረደው እርሱ ነው፤ ሁሉንም ይመላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ እርሱ ነው። 11 እርሱም ጸጋን ሰጠ፤ ከቤተ ሰቦቹም ሐዋርያትን፥ ከእነርሱም ነቢያትንና የወንጌል ሰባኪዎችን፥ ጠባቂዎችንና መምህራንን ሾመ። 12 ቅዱሳን ለአገልግሎቱ ሥራና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ እንዲጸኑ፤ 13 ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ አንድ እስክንሆን ድረስ በክርስቶስ ምልዐት መጠን፥ አካለ መጠን እንደ አደረሰ እንደ አንድ ሙሉ ሰው እስክንሆን ድረስ፥ 14 እንግዲህ በሽንገላቸው ያስቱ ዘንድ በሚተናኰሉ ሰዎች ተንኰል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ ወዲያና ወዲህ እየተፍገመገምንና እየተንሳፈፍን ሕፃናት አንሁን። 15 ነገር ግን በፍቅር እውነተኞች እንሆን ዘንድ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ። 16 ከእርሱ የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠው በሥር ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። ከአሕዛብ መለየት 17 እንግዲህ በልባቸው ከንቱ አሳብ እንደሚኖሩ እንደ አሕዛብ እንዳትኖሩ ይህን እላለሁ፤ በእግዚአብሔርም እመሰክራለሁ። 18 ልቡናቸው የተጨፈነ ነው፤ በስንፍናቸውና በድንቍርናቸው እግዚአብሔር ከሚሰጣቸው ሕይወት የተለዩ ናቸው። 19 ተስፋ የቈረጡ ናቸው፤ ራሳቸውንም ለጕስቍልና፥ ለርኵሰትና ለመዳራት አሳልፈው ሰጡ። 20 እናንተ ግን ክርስቶስን የተማራችሁት እንደዚህ አይደለም። 21 በርግጥ ከሰማችሁት፥ እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ነውና እውነትን በእርሱ ዘንድ ትማራላችሁ፤ 22 የቀድሞ ጠባያችሁን ከእናንተ አርቁ፤ ይህንም ስሕተት በሚያመጣው ምኞት ስለሚጠፋው ስለ አሮጌው ሰውነት እላለሁ። 23 የልቡናችሁን ዕውቀት አድሱ። 24 እግዚአብሔርም በእውነት፥ በቅንነትና በንጽሕና ያደሰውን አዲሱን ሰውነት ልበሱት። 25 ስለዚህም ሐሰትን ተዉአት፤ ሁላችሁም ከወንድሞቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ እኛ አንድ አካል ነንና። 26 ተቈጡ፤ አትበድሉም፤ ፀሐይ ሳይጠልቅም ቍጣችሁን አብርዱ። 27 ለሰይጣንም መንገድን አትስጡት። 28 የሚሰርቅም እንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ድሃውን ይረዳ ዘንድ በእጆቹ መልካም እየሠራ ይድከም። 29 የሚሰሙአችሁ ሞገስን ያገኙ ዘንድ፥ ግዳጃችሁ እንዲፈጸም መልካም ነገር እንጂ ክፉ ነገር ሁሉ ከአፋችሁ አይውጣ። 30 በዳናችሁ ጊዜ የታተማችሁበትን የእግዚአብሔርን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑት። 31 መራራነትንና ቍጣን፥ ብስጭትንና ርግማንን፥ ጥፋትንና ስድብን ሁሉ ከክፉ ነገር ሁሉ ጋር ከእናንተ አርቁ። 32 እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔርም በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። |