ኤፌሶን 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የጳውሎስ መታሰር 1 ስለዚህ አሕዛብ ሆይ ስለ እናንተ እኔ ጳውሎስ የክርስቶስ እስረኛው ነኝ። 2 ስለ እናንተ የሰጠኝን የእግዚአብሔርን የጸጋውን ስጦታ ሰምታችኋል። 3 አስቀድሞ በጥቂቱ እንደ ጻፍሁላችሁ ይህን ምሥጢር ገልጦ አሳይቶኛልና። 4 ይህንም በምታነቡበት ጊዜ፥ የክርስቶስን ምሥጢር ማስተዋሌን ለማወቅ ትችላላችሁ። 5 በሌላ ዘመን ለሰው ልጆች ያልተገለጠ ዛሬ ለቅዱሳን ሐዋርያቱና ለነቢያቱ በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተገለጠ፥ 6 አሕዛብን ወራሾቹና አካሉ ያደርጋቸው ዘንድ፥ በወንጌልም ትምህርት በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ተስፋ አንድ ይሆኑ ዘንድ። 7 በኀይሉ አጋዥነት እንደ ሰጠኝ እንደ ጸጋው ስጦታ መጠን እኔ መልእክተኛና አዋጅ ነጋሪ የሆንሁለት፥ 8 ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ ለእኔ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጸግነት ለአሕዛብ አስተምር ዘንድ ይህን ጸጋ ሰጠኝ። 9 ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ከዘለዓለም የተሰወረ የዚህ ምሥጢር ሥርዐትንም ለሁሉ እገልጥ ዘንድ፤ 10 ብዙ ልዩ ልዩ የሆነች የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ 11 ዓለም ሳይፈጠር የወሰናት፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም የፈጸማት፥ 12 እኛ ጸጋንና ባለሟልነትን ያገኘንበት፥ በሃይማኖት ወደሚገኘው ተስፋም ያደረሰበት፤ 13 ስለዚህም ስለ እናንተ ለክብራችሁ የምታገኘኝን መከራዬን ቸል እንዳይላት እግዚአብሔርን እማልደዋለሁ። የጳውሎስ ጸሎት 14 ስለዚህም በልቡናዬ ተንበርክኬ ለአብ እሰግዳለሁ። 15 በሰማይና በምድር ያሉ ነገዶች ሁሉ ለሚጠሩት ለእርሱ፤ 16 እንደ ጌትነቱ ምላት ይሰጣችሁ ዘንድ፥ በመንፈስ ቅዱስም ኀይል ያጸናችሁ ዘንድ። 17 በልባችሁ ውስጥ በፍቅር ሥር መሠረታችሁ የጸና ሲሆን ክርስቶስ በሃይማኖት በሰው ውስጥ ያድራልና። 18 ስፋቱና ርዝመቱ፥ ምጥቀቱና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ለማስተዋል ትችሉ ዘንድ፥ 19 የክርስቶስን ፍቅር ለመረዳት፥ በእግዚአብሔር ፍጹምነት በሁሉ ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ። 20 በከሃሊነቱ እንደ ረዳን መጠን፥ የምናስበውንና የምንለምነውን ሁሉ ትሠሩ ዘንድ፥ ታበዙም ዘንድ ሊያጸናችሁ ለሚችል፥ 21 ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ፥ በትውልድ ሁሉ ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን። |