ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሄኖክ 37 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ጻድቃን፥ እመኑ፤ ኃጥኣን ለስድብ ይሆናሉና፥ በዐመፅም ቀን ይጠፋሉና። 2 ልዑል የእናንተን ጥፋት ያስባልና፥ መላእክትም በሰማይ በእናንተ ጥፋት ላይ ደስ ይላቸዋልና ይህ የታወቀ ይሆንላችኋል። 3 ኃጥኣን፥ ምን ታደርጉ ዘንድ አላችሁ? የጻድቃን የጸሎታቸውን ቃል በምትሰሙበት ጊዜ በዚያች የፍርድ ቀን ወዴት ትሸሻላችሁ? 4 በእነዚያም ወራቶች የቅዱሳን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ትደርሳለች፥ በእናንተ ግን የቅጣታችሁ ወራት ይደርስባችኋል። 5 የዐመፃችሁም ነገር ሁሉ በገናናውና በቅዱሱ ፊት ይነበባል፤ ፊታችሁም ያፍራል፤ በዐመፅ የጸና ሥራ ሁሉ ይጣላል። 6 በባሕርና በየብስ መካከል ያላችሁ፥ ክፉ መታሰቢያችሁም በላያችሁ ያለባችሁ ኃጥኣን ወዮላችሁ! 7 በእውነት ያይደለ ብርንና ወርቅን የምትሰበስቡ፥ ባለጸግነትን በለጸግን፤ ገንዘብም በዛልን፤ የወደድነውንም ሁሉ ገንዘብ አደረግን የምትሉ እናንተ፥ ወዮላችሁ! 8 ብሩን ሰብስበን በሳጥኖቻችን መልተናልና፥ በቤታችንም ያሉ አራሾች እንደ ውኃ በዝተውልናልና አሁን ያሰብነውን እናድርግ የምትሉ እናንተ ወዮላችሁ! 9 ሐሰታችሁ እንደ ውኃ ይፈስሳል፤ ባለጠግነታችሁ አይኖርላችሁምና፤ ነገር ግን ከእናንተ ፈጥኖ ይጠፋል። ሁሉን በዐመፅ ሰብስባችሁታልና። 10 እናንተም ለታላቅ ርግማን ትሰጣላችሁ። 11 ዛሬም እኔ ለብልሆችና ለሰነፎች እምልላችኋለሁ፤ በምድር ላይ ብዙ ነገርን ታያላችሁና። 12 እናንተ ወንዶቹ ከሴቶች ይልቅ ጌጥን ታጌጣላችሁና፥ ይልቁንም ከድንግሊቱ ይልቅ ብዙ መልክ ያለውን ጌጥ ታደርጋላችሁና። 13 በመንግሥትና በገናናነት፥ በሥልጣንም፥ በብርና በወርቅ፥ በነጭ ሐርም፥ በክብርም ታጌጣላችሁ። 14 መብሎችም እንደ ውኃ ይፈስሳሉ፤ ስለዚህም ትምህርትና ጥበብ የላቸውም። 15 በዚያም ከገንዘባቸውና ከጌትነታቸው፥ ከክብራቸውም ሁሉ ጋር አንድ ሆነው ይጠፋሉ። 16 በስድብና በችጋር፥ በታላቅ በቀልም ነፍሳቸው ወደ እሳት ጕድጓድ ትወድቃለች። 17 ኃጥኣን፥ ተራራው ወንድ ባሪያ እንዳልነበረ፥ እንግዲህም ወዲህ እንደማይሆን፥ ኮረብታም ለሴት ሴት ባሪያ እንዳይደለች ለእናንተ ማልሁላችሁ። 18 እንደዚሁም ኀጢአት በምድር ላይ አልተላከችም፤ ነገር ግን ሰዎች ከራሳቸው ፈጠሩአት፤ እርሷንም የሠሯት ሰዎች ለታላቅ መርገም ይሆናሉ። 19 ለሴትም ምክነት አልተሰጣትም፤ ነገር ግን በእጅዋ በሠራችው ሥራ ልጅ ሳትወልድ ትሞታለች። 20 ኃጥኣን፥ በቅዱሱና በገናናው ማልሁላችሁ፤ ክፉ ሥራችሁ ሁሉ በሰማያት የተገለጠ ነውና፥ የተከደነና የተሰወረ የግፍ ሥራም የላችሁምና። 21 በመንፈሳችሁ አታስመስሉ፤ በሰማይም በልዑል ፊት በየቀኑ ይጻፍ ዘንድ ያለውን ኀጢአታችሁን ሁሉ እንደማታውቁና እንደማታዩ በልቡናችሁ አትናገሩ። 22 የምትሠሩትም ግፍ ሁሉ በየቀኑ እስከ ፍርዳችሁ ቀን ይጻፋልና ከዛሬ ጀምሮ ታውቃላችሁ። 23 ሰነፎች፥ ወዮላችሁ! በስንፍናችሁ ትጠፋላችሁና፥ ጠቢባንንም አትሰሟቸውምና፥ በጎ ነገርም አታገኛችሁምና። 24 አሁንም ለጥፋት ቀን የተዘጋጃችሁ እንደ ሆናችሁ ዕወቁ፥ ኃጥኣን ተፈርዶባችሁ ትሄዳላችሁ እንጂ እንድናለን ብላችሁ ተስፋ አታድርጉ። 25 መድንን አታውቁምና ትሞታላችሁ። በነፍሳችሁ ለታላቅዋ የፍርድ ቀን፥ ለታላቅዋ የመከራና የጕስቍልና ቀንም ተዘጋጅታችኋልና። 26 ክፉ ሥራን የምትሠሩ፥ ብርንዶንም የምትበሉ ልበ ደንዳኖች ወዮላችሁ! በልታችሁና ጠጥታችሁ የምትጠግቡትን መልካሙን ነገር ከየት አገኛችሁ? ልዑል እግዚአብሔር በምድር ላይ ካበዛው መልካም ሁሉ አይደለምን? ነገር ግን ሰላም የላችሁም። 27 የዐመፅን ሥራ የምትወዷት ወዮላችሁ! በጎዋን ነገር ለእናንተ ለምን ተስፋ ታደርጋላችሁ? 28 በጻድቃንም እጆች ተላልፋችሁ ትሰጡ ዘንድ እንዳላችሁ ዕወቁ፤ አንገቶቻችሁንም ቈርጠው ይገድሏችኋል፤ አይራሩላችሁምም። 29 በጻድቃን መከራ ደስ የሚላችሁ ወዮላችሁ! ለእናንተ መቃብር አይቈፈርላችሁምና። 30 የጻድቃንን ነገር የምትንቁ ወዮላችሁ! የሕይወት ተስፋ አይሆንላችሁምና። 31 ሐሰት ነገርንና የዝንጉዎችን ነገር የምትጽፉ ወዮላችሁ! እነርሱ ስንፍናን እንዲሰሟትና እንዳይዘነጓት ሐሰታቸውን ይጽፋሉና። 32 ሰላምም አይሆንላቸውም፤ ነገር ግን ሳይዘገዩ ፈጥነው ሞትን ይሞታሉ። 33 ኀጢአትን የምትሠሩ፥ የሐሰትን ነገር የምታመሰግኑና የምታከብሩም ወዮላችሁ! በዚሁም ጠፋችሁ፤ ሕይወትና በጎ ነገርም የላችሁም። 34 የቅን ፍርድ ነገሮችን የሚለዋውጡ ወዮላቸው! የዘለዓለም ሥርዐትንም ይለውጣሉ፤ ራሳቸውንም ኀጢአተኞች እንዳልሆኑ የሚያደርጉ በምድር ላይ ይረገጡ ዘንድ አላቸው። |