Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ሄኖክ 36 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)

1 አሁንም ልጆቼ፥ እላችኋለሁ፤ ጽድቅን ውደዱአት፤ በእርሷም ሂዱ፤ የጽድቅ መንገዶችን ይቀበሏቸው ዘንድ ይገባልና፤

2 የዐመፅ መንገዶችም ፈጥነው ይጠፋሉ፤ ያንሳሉም፤ ለታወቁ ሰዎችም ከልጅ ልጅ ጀምሮ የዐመፅና የሞት መንገዶች ይገለጣሉ፤ ከእነርሱም ይርቃሉ፤ አይከተሏቸውምም።

3 አሁንም ለእናንተ ለጻድቃን እላችኋለሁ፤ በክፉ መንገዶች አትሂዱ፤ በግፍዕና በሞት መንገድም አትሂዱ፤ እንዳትጠፉም ወደ እነርሱ አትቅረቡ፤ ነገር ግን የተመረጠች ጽድቅንና ሕይወትን ለእናንተ ፈልጉ፤ ምረጡም።

4 በሰላም መንገዶችም ሂዱ፤ ትድናላችሁ፤ በተድላም ትኖራላችሁ፤ በልቡናችሁም ዐሳብ ትይዛላችሁ።

5 ክፉ ጥበብን ይሠሩ ዘንድ ኃጥኣን ሰዎችን እንደሚፈትኗቸው አውቃለሁና ነገሬ ከልቡናቸሁ አይጥፋ፤ ቦታም ሁሉ አይገኝላትም፤ መከራም ሁሉ አይጐድልም።

6 ዐመፅንና ግፍን ለሚያንጹ፥ ተንኰልንም ለሚሠሯት ሰዎች ወዮላቸው! እነርሱ ፈጥነው ይጠፋሉና፥ ሰላምም የላቸውምና።

7 ቤታቸውን በኀጢአት ለሚሠሩ ሰዎች ወዮላቸው! ከመሠረታቸው ሁሉ ይጠፋሉና፥ በሰይፍም ይወድቃሉና፥ ወርቅንና ብርንም የሚሰበስቧት በፍርድ ፈጥነው ይጠፋሉና።

8 እናንተ ባለጠጎች ወዮላችሁ! በባለጠግነታችሁ ላይ ታምናችኋልና፥ ከባለጠግነታችሁም ትለያላችሁና።

9 በባለጠግነታችሁ ወራት ልዑልን አላሰባችሁትምና፥ እናንተስ ስድብን፥ በደልንም ሠራችኋት፤ ደም ለሚፈስባት ቀንና ለጨለማዋ ቀን፥ ለታላቅዋ ፍርድ ቀንም የተዘጋጃችሁ ሆናችኋል።

10 የፈጠራችሁ እንደሚያጠፋችሁ፥ በውድቀታችሁም ላይ ይቅርታው እንደማይደረግላችሁ እኔ እንደዚህ ብዬ እነግራችኋለሁ።

11 ፈጣሪያችሁም በጥፋታችሁ ደስ ይለዋል፤ የእናንተም ጻድቃን በእነዚያ ወራት ለዝንጉዎችና ለኃጥኣን መዘባበቻ ይሆናሉ።

12 ዐይኖቼ ውኃን የቋጠሩ ደመናዎችን ይሆኑ ዘንድ፥ በእናንተም ላይ አለቅስ ዘንድ፥ ውኃንም እንደ ቋጠረ ደመና እንባዬን አፈስ ዘንድ፥ ከልቡናዬ ኀዘንም አርፍ ዘንድ ማን በሰጠኝ ነበር።

13 ስድብንና ክፋትን ታደርጉ ዘንድ ማን ሰጣችሁ? እናንተን ኃጥኣንን ቍርጥ ፍርድ ያገኛችኋል።

14 ጻድቃን ከኃጥኣን የተነሣ አትፍሩ፤ እንደ ወደዳችሁ በእነርሱ ላይ ፍርድን ታደርጉባቸው ዘንድ እግዚአብሔር ዳግመኛ በእጃችሁ ይጥላቸዋልና።

15 እንዳትፈቱ ሆናችሁ ግዝትን ለምትገዝቱ ለእናንተ ወዮላችሁ! ስለ ኀጢአታችሁም ድኅነት ከእናንተ ራቀ።

16 ለባልንጀራችሁ ክፉ ምላሽ ለምትመልሱ ለእናንተ ወዮላችሁ! እንደ ሥራችሁ መጠን ፍዳውን ትቀበላላችሁና።

17 ሐሰት ለምትመሰክሩ፥ ለበደልም ለምትገቧት ለእናንተ ወዮላችሁ! ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁና።

18 እናንተ ኃጥኣን፥ ወዮላችሁ! ጻድቃንን ታሳድዱአቸዋላችሁና፥ እናንተም በእነርሱ እጅ ትወድቃላችሁና፥ ከዐመፅም የተነሣ ትሰደዳላችሁና፥ የእነርሱም ቀንበር በእናንተ ይጸናልና።

19 ጻድቃን፥ ይህን ተስፋ አድርጉ፤ ኃጥኣን ከፊታችሁ ፈጥነው ይጠፋሉና፥ እንደ ወደዳችሁም ሥልጣን በእነርሱ ላይ ይሆንላችኋልና።

20 ኃጥኣንም መከራ በሚቀበሉበት ቀን የእናንተ ልጆች እንደ አሞሮች ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ይነሣሉ።

21 ማረፊያችሁም ከጥንብ አሞራ ቦታ ይልቅ ይርቃል፤ ወጥታችሁም ከዐመፀኞች ፊት የተነሣ ወደ ጕድጓድና ወደ ዐለቱ ንቃቃት እንደ ሽኮኮ ለዘለዓለም ትገባላችሁ።

22 በእናንተም ላይ ይጮኻሉ፤ ይህ ኀጢአታችሁ በእናንተ ምስክር ይሆንባችኋል እንጂ እናንተ እንደ እነርሱ አትሆኑም፤ ከኃጥኣንም ጋር አንድ ሆናችሁ፤ እንደ ሄለይም ያለቅሳሉ።

23 መከራን የምትቀበሉ እናንተ ግን አትፍሩ፤ ድኅነት ይሆንላችኋልና፥ የበራ ብርሃንም ለእናንተ ያበራላችኋልና፥ ከሰማይም የዕረፍት ቃልን ትሰማላችሁና።

24 ኃጥኣን ወዮላችሁ! ባለጸግነታችሁ ጻድቃንን ያስመስላችኋልና፥ ልቡናችሁም ኃጥኣን እንደ ሆናችሁ ይዘልፋችኋልና።

25 ይህም ነገር ለክፋታችሁ መታሰቢያ በእናንተ ላይ ምስክር ይሆናል።

26 የስንዴውን ፍሬ የምትበሉ፥ ከምንጩም መነሻ ኀይልን የምትጠጡ፥ የተዋረዱትንም በኀይላችሁ የምትረጋግጧቸው ወዮላችሁ!

27 ሁልጊዜ ውኃን የምትጠጡ ወዮላችሁ! ፍዳን ፈጥናችሁ ትቀበላላችሁና፥ የሕይወትንም ምንጭ ትታችኋልና ፈጽማችሁ ትጠፋላቸሁ።

28 ዐመፅንና ሽንገላን፥ ፅርፈትንም የምትሠሩ ወዮላችሁ! ይህም በእናንተ ላይ ለክፋት መታሰቢያ ይሆናል።

29 ጻድቁን በኀይል የምትቀጠቅጡት ኀያላን ወዮላችሁ! የጥፋታችሁ ቀን ትመጣለችና።

30 በእነዚያም ወራቶች በፍርዳችሁ ቀን ብዙዎችና ደጎች ወራቶች ለጻድቃን ይመጣሉ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች