መክብብ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለሁሉ ጊዜ አለው 1 ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከፀሐይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። 2 ለመፅነስ ጊዜ አለው፥ ለመውለድም ጊዜ አለው፤ ለመኖር ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው። 3 ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ 4 ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው። 5 ድንጋይን ለመወርወር ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ 6 ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ 7 ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ 8 ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። 9 ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድን ነው? 10 እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ድካም ሁሉ አይቻለሁ። 11 የሠራው ሥራ ሁሉ በጊዜው መልካም ነው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘለዓለምነትን በልቡ ሰጠው። 12 ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር በውስጣቸው መልካም ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። 13 ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ መልካምን ያይ ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 14 እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘለዓለም እንዲኖር ዐወቅሁ፤ በእነርሱም ላይ መጨመር ከእነርሱም ማጕደል አይቻልም፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ። 15 በፊት የተደረገው አሁን አለ። ይደረግ ዘንድ ያለውም እነሆ ተደርጓል፤ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል። 16 ደግሞም ከፀሐይ በታች በጻድቅ ስፍራ ኃጥእ፥ በኃጥእም ስፍራ ጻድቅ እንዳለ አየሁ። 17 እኔም በልቤ፥ “በዚያ ለነገር ሁሉና ለሥራ ሁሉ ጊዜ አለውና በጻድቁና በኀጢአተኛው ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል” አልሁ። 18 እኔ በልቤ ስለ ሰው ልጆች ነገር፥ “እንደ እንስሳ መሆናቸውን ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” አልሁ። 19 ለሰው ልጆች ሞት አለባቸው፥ ለእንስሳም ሞት አለባቸው፤ አንድ ሞት አለባቸው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ ለሁሉም አንድ እስትንፋስ አላቸው፥ ሰው ከእንስሳ ብልጫው ምንድን ነው? ሁሉም ከንቱ ነውና ምንም የለውም። 20 ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ተገኘ፥ ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል። 21 የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣ፥ የእንስሳም ነፍስ ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው? 22 ያም ዕድል ፋንታው ነውና ሰው በሥራው ደስ ከሚለው በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለው አየሁ፤ ከእርሱ በኋላስ የሚሆነውን ያይ ዘንድ የሚያመጣው ማን ነው? |