ዘዳግም 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “የወንድምህ በሬ ወይም በግ በመንገድ ጠፍቶ ብታይ ቸል አትበል፤ እነርሱን መልሰህ ለወንድምህ ስጥ። 2 ወንድምህም በአቅራቢያህ ባይሆን ወይም ባታውቀው ይዘሃቸው ወደ ቤትህ ትገባለህ፤ ወንድምህ እስኪሻቸው ድረስ በአንተ ዘንድ ይቀመጣሉ፤ ለእርሱም ትመልስለታለህ። 3 አህያውም ቢሆን፥ በሬውም ቢሆን፥ ወይም ልብሱ ቢሆን እንዲሁ ታደርጋለህ፤ እንዲሁም በወንድምህ በጠፋበት ነገር ሁሉ ባገኘኸው ጊዜ ታደርጋለህ፤ ቸል ልትለው አይገባህም። 4 የወንድምህ አህያው ወይም በሬው በመንገድ ወድቆ ብታይ ቸል አትበላቸው፤ ነገር ግን ከእርሱ ጋር ሆነህ አነሣሣው። 5 “ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፤ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፤ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና። 6 “በመንገድ በማናቸውም ዛፍ ላይ ወይም በመሬት ላይ ከጫጭቶችና ከእንቍላል ጋር እናቲቱ በእነዚህ ላይ ተቀምጣ የወፍ ጎጆ ብታገኝ እናቲቱን ከጫጭቶችዋ ጋር አትውሰድ። 7 ነገር ግን መልካም ይሆንልህ ዘንድ፥ ዕድሜህም ይረዝም ዘንድ እናቲቱን ልቀቅ፤ ጫጭቶችንም ለአንተ ውሰድ። 8 “አዲስ ቤት በሠራህ ጊዜ ማንም ከእርሱ ወድቆ በቤትህ ግድያ እንዳታደርግ ለሰገነትህ መከታ አድርግለት። 9 “ፍሬውንና የዘራኸውን ዘር ከወይንህ ፍሬ ጋር እንዳትለቅም በወይንህ ቦታ ላይ የተለያየ ዓይነት ተክል አትትከል። 10 በአህያህና በበሬህ በአንድነት አትረስ። 11 ከተልባ እግርና ከበግ ጠጕር በአንድነት የተሠራ ልብስ አትልበስ። 12 “በምትለብሰው በልብስህ በአራቱ ማዕዘን ዘርፍ አድርግ። ድንግልናን ስለ መጠበቅ 13 “ማናቸውም ሰው ሚስት ቢያገባ፥ አብሮአትም ከኖረ በኋላ ቢጠላት፥ 14 የነውር ነገርም ቢያመጣባት፥ እኔ ይህችን ሴት ሚስቴ አድርጌ አገባኋት፤ በደረስሁባትም ጊዜ ድንግልናዋን አላገኘሁባትም ብሎ ክፉ ስም ቢያወጣባት፥ 15 የብላቴናዪቱ አባትና እናት የልጃቸውን የድንግልናዋን ልብስ ወስደው በበሩ አደባባይ ወደ ተቀመጡ ወደ ከተማ ሽማግሌዎች ያምጡት፤ 16 የብላቴናዪቱም አባት ሽማግሌዎቹን፦ እኔ ለዚህ ሰው ልጄን ዳርሁለት፤ እርሱም ጠላት፤ 17 እነሆም፦ በልጅህ ድንግልና አላገኘሁባትም ብሎ የነውር ነገር አወራባት፤ የልጄም የድንግልናዋ ልብስ ይኸው ይላቸዋል። በከተማም ሽማግሌዎች ፊት ልብሱን ይዘረጋሉ። 18 የዚያች ከተማ ሽማግሌዎችም ያን ሰው ወስደው ይገሥጹት፤ 19 በእስራኤል ድንግል ላይ ክፉ ስም አምጥቶአልና መቶ የብር ሰቅል ያስከፍሉት፤ ለብላቴናዪቱም አባት ይስጡት፤ እርስዋም ሚስት ትሁነው፤ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም። 20 “ነገሩ ግን እውነት ቢሆን፥ የብላቴናዪቱም ድንግልናዋ ባይገኝ፥ 21 ብላቴናዪቱን ወደ አባቷ ቤት ደጅ ያውጡአት፤ በእስራኤልም ዘንድ ስንፍናን አድርጋለችና፥ የአባቷንም ቤት አስነውራለችና የከተማው ሰዎች በድንጋይ ወግረው ይግደሉአት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ። 22 “ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፥ አመንዝራውና አመንዝራዪቱ ሁለታቸው ይገደሉ፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከእስራኤል ታስወግዳለህ። 23 “ለወንድ የታጨች ድንግል ልጅ ብትኖር፥ ሌላ ሰውም በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርስዋ ጋር ቢተኛ፥ ሁለቱን ወደዚያች ከተማ በር አውጡአቸው፤ 24 ብላቴናዪቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና፥ ሰውየውም የባልጀራውን ሚስት አስነውሮአልና በድንጋይ ወግረው ይግደሉአቸው፤ እንዲሁ ክፉውን ነገር ከውስጥህ ታስወግዳለህ። 25 “ነገር ግን ሰው የታጨችውን ልጃገረድ በሜዳ ቢያገኛት፥ በግድ አሸንፎም ቢደርስባት፥ ያ የደረሰባት ሰው ብቻውን ይገደል። 26 በብላቴናዪቱ ላይ ግን ምንም አታድርጉ፤ በብላቴናዪቱ ላይ ለሞት የሚያበቃ ኀጢአት የለባትም፤ ሰው በባልንጀራው ላይ ተነሥቶ እንደሚገድለው ይህ ነገር ደግሞ እንደዚሁ ነውና፤ 27 በሜዳ ባገኛት ጊዜ የታጨችው ልጃገረድ ጮኻለችና፥ የሚታደጋትም አልነበረምና። 28 ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ያልታጨች ልጃገረድ ቢያገኝ፥ በግድ አሸንፎ ቢደፍራት፥ ቢያገኙትም፥ 29 ያ የደፈራት ሰው አምሳ የብር ሰቅል ለብላቴናዪቱ አባት ይስጥ፤ አስነውሮአታልና ሚስት ትሁነው፤ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም። 30 “ማናቸውም ሰው የእንጀራ እናቱን አይውሰድ፤ የአባቱንም ኀፍረት አይግለጥ። |