ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ትንቢተ ዳንኤል 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳንኤል ጸሎት 1 በከለዳውያን መንግሥት ላይ በነገሠ፥ ከሜዶን ዘር በነበረ በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያው ዓመት፥ 2 በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል በሰባ ዓመት የኢየሩሳሌም ጥፋት እንደሚፈጸም እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ቃል በተጻፈበት መጽሐፍ ያለውን የዘመኑን ቍጥር ዐወቅሁ። 3 ማቅ ለብሼ፥ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ። 4 ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፤ ተናዝዤም እንዲህ አልሁ፥ “ጌታ ሆይ! ከሚወድዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፈራ አምላክ ሆይ! 5 ኀጢአትን ሠርተናል፥ በድለንማል፤ ክፋትንም አድርገናል፤ ዐምፀንማል፤ ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፤ 6 በስምህም ለነገሥታቶቻችንና ለአለቆቻችን፥ ለአባቶቻችንም፥ ለሀገሩም ሕዝብ ሁሉ የተናገሩትን ባሪያዎችህን ነቢያትን አልሰማንም። 7 ጌታ ሆይ! ጽድቅ ለአንተ ነው፤ እንደ ዛሬም ለእኛ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ፥ ለእስራኤልም ሁሉ በቅርብና በሩቅም ላሉት አንተን በበደሉበት በበደላቸው ምክንያት በበተንህበት ሀገር ሁሉ የፊት እፍረት ነው። 8 ጌታ ሆይ! በአንተ ላይ ኀጢአት ስለ ሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን፥ ለአለቆቻችንና ለአባቶቻችንም የፊት እፍረት ነው። 9 ለጌታ ለአምላካችን ምሕረትና ይቅርታ ነው፤ በእርሱ ላይ ዐምፀናልና። 10 በባሪያዎቹም በነቢያት እጅ በፊታችን በአኖረው በሕጉ እንሄድ ዘንድ የአምላካችንን የግዚአብሔርን ቃል አልሰማንምና። 11 እስራኤልም ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፤ ቃልህንም መስማትን እንቢ ብለዋል፤ በእርሱ ላይ ኀጢአት ሠርተናልና መርገምና በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላ መጣብን። 12 እጅግ ክፉ ነገርንም በእኛ ላይ በማምጣቱ በላያችንና በእኛ ዘንድ በተሾሙት ፈራጆቻችን ላይ የተናገረውን ቃል አጸና፤ በኢየሩሳሌምም ላይ እንደ ተደረገው ያለ ነገር ከቶ ከሰማይ ሁሉ በታች አልተደረገም። 13 በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈ ይህ ክፉ ነገር ሁሉ መጣብን፤ ከኀጢአታችን እንመለስ፤ እውነትህንም እናስብ ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት አልለመንንም። 14 ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ ነገርን በእኛ ላይ ፈጥኖ አመጣ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በሚሠራው ሥራ ሁሉ ጻድቅ ነውና፤ እኛም ቃሉን አልሰማንምና። 15 አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በበረታች እጅ ያወጣህ፥ እንደ ዛሬም ቀን ስምን ለአንተ ያደረግህ ጌታ አምላካችን ሆይ! ኀጢአትን ሠርተናል፤ ክፋትንም አድርገናል። 16 ጌታ ሆይ! በፍጹም ቸርነትህ ቍጣህንና መቅሠፍትህን ከከተማህ ከኢየሩሳሌምና ከተቀደሰው ተራራህ መልስ፤ ስለ ኀጢአታችንና ስለ አባቶቻችን በደል ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋልና። 17 አሁንም አምላካችን ሆይ! የባሪያህን ጸሎትና ልመናውን ስማ፤ ጌታ ሆይ! በፈረሰው በመቅደስህ ላይ ስለ አንተ ስትል ፊትህን አብራ። 18 አምላኬ ሆይ! በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህንም ገልጠህ ጥፋታችንንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት። 19 አቤቱ! ስማ፤ አቤቱ፥ ይቅር በል፤ አቤቱ! አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ! ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና ስለ ራስህ አትዘግይ።” 20 እኔም ገና ስናገርና ስጸልይ፥ በኀጢአቴና በሕዝቤም በእስራኤል ኀጢአት ስናዘዝ፥ በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ይቅርታን ስጠይቅ፥ 21 ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይችው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ፤ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ። 22 አስተማረኝም፤ ተናገረኝም፤ እንዲህም አለ፥ “ዳንኤል ሆይ! ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ። 23 አንተ እጅግ የተወደድህ ሰው ነህና በልመናህ መጀመሪያ ላይ ቃል ወጥቶአል፤ እኔም እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፤ አሁንም ነገሩን መርምር፤ ራእዩንም አስተውል። 24 “ዐመፃን ይጨርስ፥ ኀጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘለዓለምንም ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል። 25 ስለዚህ ዕወቅ፤ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ ጎዳናዋና ቅጥርዋ ተመልሶ ይሠራል፤ ጊዜውም ይፈጸማል። 26 ከስድሳ ሁለት ሱባዔ በኋላም መሢሕ ይገደላል፤ በእርሱም ዘንድ ፍትሕ የለም፤ ከሚመጣውም አለቃ ጋር ከተማዪቱንና መቅደሱን ያጠፋል፤ ፍጻሜውም በጎርፍ ይሆናል፤ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል። 27 እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያጸናል፤ በሱባዔውም እኩሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በቤተ መቅደስም የጥፋት ርኵሰት ይሆናል፤ እስከ ዘመኑም ፍጻሜ የጥፋት መጨረሻ ይሆናል።” |