ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ትንቢተ ዳንኤል 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ 4 አራዊት ራእይ 1 በባቢሎን ንጉሥ በብልጣሶር በመጀመሪያው ዓመተ መንግሥት ዳንኤል በአልጋው ላይ ሕልምንና የራሱን ራእይ አየ፤ ከዚያም በኋላ ሕልሙን ጻፈ፥ 2 እንዲህም አለ፥ “እኔ ዳንኤል ራእይ አየሁ፤ እነሆም አራቱ የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ይነፍሱ ነበር። 3 አራትም ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ፥ እያንዳንዲቱም ከሌላይቱ ልዩ ነበረች። 4 መጀመሪያይቱ እንደ ሴት አንበሳ ነበረች፤ እንደ ንስርም ክንፍ ነበራት፤ ክንፎችዋም ከእርስዋ እስኪነቀሉ ድረስ አይ ነበር፤ ከምድርም ከፍ ከፍ አለች፤ እንደ ሰውም በእግር ቆመች፤ የሰውም ልብ ተሰጣት። 5 እነሆም ሁለተኛይቱ ድብ የምትመስል ሌላ አውሬ ነበረች፤ በአንድ ወገንም ቆመች፤ ሦስትም የጎድን አጥንቶች በአፍዋ ውስጥ በጥርሶችዋ መካከል ነበሩ፤ እንደዚህም፦ ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ አሏት። 6 ከዚህም በኋላ፥ እነሆ ነብር የምትመስል፥ በጀርባዋም ላይ አራት የወፍ ክንፎች የነበሩአት፤ ሌላ አውሬ አየሁ፤ ለአውሬይቱም አራት ራሶች ነበሩአት፤ ሥልጣንም ተሰጣት። 7 ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም የምታስፈራና የምታስደነግጥ፥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ ዐሥር ቀንዶችም ነበሩአት። 8 ቀንዶችንም ተመለከትሁ፤ እነሆም፤ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፤ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ፤ እነሆም በዚያ በትንሹ ቀንድ እንደ ሰው ዐይኖች የነበሩ ዐይኖች፥ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት። 9 “ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፤ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ነጭ ሱፍ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። 10 የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፤ ሺህ ጊዜ ሺህ የሆኑ ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ለፍርድም ተቀመጠ፤ መጻሕፍትንም ገለጠ። 11 የዚያን ጊዜም ይህ ቀንድ ከተናገረው ነገር የተነሣ አውሬው እስኪርቅና እስኪጠፋ ድረስ አየሁ፤ በእሳትም ያቃጥሉት ዘንድ ሰውነቱን አሳልፈው ሰጡት፤ 12 ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፤ የሕይወታቸው ዘመን ግን እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ረዘመ። 13 “በሌሊትም ራእይ አየሁ፤ እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና መጣ፤ በዘመናትም ወደ ሸመገለው ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። 14 ወገኖችና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር፥ መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው። የሕልሙ ፍች 15 “እኔም ዳንኤል መንፈሴ ተንቀጠቀጠብኝ፤ ከራሴም ራእይ የተነሣ ልቤ ደነገጠብኝ። 16 በዚያም ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ ስለዚህ ሁሉ እውነቱን ጠየቅሁት፤ እርሱም ነገረኝ፤ የነገሩንም ፍቺ አስታወቀኝ፥ እኔም ነገሩን ተረዳሁት። 17 እንዲህም አለኝ፦ እነዚህ ያየሃቸው አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ አራት ነገሥታት ናቸው፤ ዳግመኛም ይወገዳሉ። 18 ነገር ግን መንግሥት ለልዑሉ ቅዱሳን ይመለሳል፤ የልዑሉ ቅዱሳንም መንግሥቱን ይወስዳሉ፤ እስከ ዘለዓለም ዓለምም መንግሥቱን ይወርሳሉ። 19 ከዚህም በኋላ ከቀሩት ሁሉ ተለይታ እጅግ ስለምታስፈራው፥ ጥርሶችዋም የብረት፥ ጥፍሮችዋም የናስ ስለ ሆኑት፥ ስለምትበላውና ስለምታደቅቀው፥ የቀረውንም በእግርዋ ስለምትረግጠው ስለ አራተኛዪቱ አውሬ፥ 20 በራስዋም ላይ ስለ ነበሩ ስለ ዐሥር ቀንዶች፥ በኋላም ስለ ወጣው፥ በፊቱም ስለ ወደቁ ሦስቱ ቀንዶች፥ ዐይኖችና ትዕቢት የተናገረ አፍ ስለ ነበሩት ራሱም ከሌሎች ስለ በለጠ ስለ ሌላው ቀንድ እውነቱን ለማወቅ ጠየቅሁት። 21 እነሆም፥ ያ ቀንድ ከቅዱሳን ጋር ሲዋጋ አየሁ፤ አሸነፋቸውም፤ 22 በዘመናት የሸመገለው እስኪመጣ ድረስ፥ ፍርድም ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪሰጥ ድረስ፥ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወስዱበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ አሸነፋቸው። 23 “እንዲህም አለኝ፦ አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሣ አራተኛ መንግሥት ነው፤ እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ ይበልጣል። ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፤ ይረግጣታል፤ ያደቅቃትማል። 24 ዐሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነርሱም በኋላ ሌላ ይነሣል፤ እርሱም ከፊተኞቹ በክፋት የበለጠ ይሆናል፤ ሦስቱንም ነገሥታት ያዋርዳል። 25 በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፤ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፤ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኩሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ። 26 ነገር ግን ፍርድ ይሆናል፤ እስከ ፍጻሜውም ድረስ ያፈርሱትና ያጠፉት ዘንድ ግዛቱን ያስወግዱታል። 27 መንግሥትም፥ ግዛትም፥ ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘለዓለም መንግሥት ነው፤ መኳንንቱም ሁሉ ይገዙለታል፤ ይታዘዙለትማል።” 28 የነገሩም ፍጻሜ እስከዚህ ድረስ ነው። እኔም ዳንኤል በአሳቤ እጅግ ተቸገርሁ፤ ፊቴም ተለወጠብኝ፤ ዳሩ ግን ነገሩን በልቤ ጠብቄአለሁ። |