ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ትንቢተ ዳንኤል 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በዳንኤል ላይ የተደረገ ሤራ 1 ዳርዮስም በመንግሥቱ ሁሉ ዘንድ እንዲሆኑ መቶ ሃያ መሳፍንትን በመንግሥቱ ላይ ይሾም ዘንድ ወደደ። 2 መሳፍንቱም ግብሩን ያመጡላቸው ዘንድ፥ ንጉሡም በማንኛውም እንዳይቸገር ሦስት አለቆች በላያቸው አደረገ፤ ከእነርሱም አንደኛው ዳንኤል ነበረ። 3 ዳንኤልም መልካም መንፈስ ስለ አለው ከአለቆችና ከመሳፍንት በለጠ፤ ንጉሡም በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ሾመው። 4 ያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ምክንያት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የታመነ ነበረና፥ ምንም በደል አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም። 5 እነዚያም ሰዎች፥ “ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ምክንያት አናገኝበትም” አሉ። 6 ያን ጊዜም ሹሞቹና መኳንንቱ ወደ ንጉሡ ተሰብስበው እንዲህ አሉት፥ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር። 7 የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ ሹሞችና መሳፍንት፥ አማካሪዎችና አዛዦች፦ ንጉሥ ሆይ! ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፥ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ይጣል የሚል የንጉሥ ሕግና ብርቱ ትእዛዝ ይወጣ ዘንድ ተማከሩ። 8 አሁንም ንጉሥ ሆይ! እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እንዳይለወጥ ትእዛዙን አጽና፤ ጽሕፈቱንም ጻፍ።” 9 ያን ጊዜም ንጉሡ ዳርዮስ ይህን ሥርዐት ይጽፉ ዘንድ አዘዘ። ዳንኤል በአንበሳ ጕድጓድ እንደ ተጣለ 10 ዳንኤልም ይህ ሥርዐት እንደ ታዘዘ በዐወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፤ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ ከቀኑ በሦስት ሰዓት በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም። 11 እነዚያም ሰዎች በማንኛውም ነገር ዘወትር ይመለከቱት ነበርና ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። 12 ወደ ንጉሡም ቀርበው ስለ ንጉሡ ትእዛዝ፥ “ንጉሥ ሆይ! ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን?” አሉት። ንጉሡም መልሶ፥ “ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው” አላቸው። 13 የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው፥ “ንጉሥ ሆይ! ከይሁዳ የምርኮ ልጆች የሆነው ዳንኤል ከቀኑ በሦስት ሰዓት ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም” አሉት። 14 ንጉሡም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ፤ ያድነውም ዘንድ ልቡን ወደ ዳንኤል አደረገ፤ ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ። 15 ያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ወደ ንጉሡ ተሰብስበው ንጉሡን፥ “ንጉሥ ሆይ! ንጉሡ ያጸናው ትእዛዝ ወይም ሥርዐት ይለወጥ ዘንድ እንዳይገባ የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንደ ሆነ ዕወቅ” አሉት። 16 ያን ጊዜም ዳንኤልን አምጥተው በአንበሶች ጕድጓድ ይጥሉት ዘንድ ንጉሡ አዘዘ፤ ንጉሡም ዳንኤልን፥ “ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ እርሱ ያድንህ” አለው። 17 ድንጋይም አምጥተው በጕድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የሚተነኳኰል ሰው እንዳይኖር በቀለበቱና በመኳንንቱ ቀለበት አተመው። 18 ንጉሡም ወደ ቤቱ ሄደ፤ ሳይበላም ተኛ፤ የሚበላውም አላመጡለትም፤ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ። እግዚአብሔርም የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤ ዳንኤልንም አልቧጨሩትም። ዳንኤል ከአንበሶች አፍ እንደ ዳነ 19 በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሣ፤ ፈጥኖም ወደ አንበሶች ጕድጓድ ሄደ። 20 ወደ ጕድጓዱም በቀረበ ጊዜ በታላቅ ቃል ጮኸ፤ ንጉሡም ዳንኤልን፥ “የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ! ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች አፍ ያድንህ ዘንድ ችሎአልን?” አለው። 21 ዳንኤልም ንጉሡን፥ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር። 22 በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፤ ንጉሥ ሆይ! አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፤ እነርሱም አልቧጨሩኝም” አለው። 23 ያን ጊዜም ንጉሡ እጅግ ደስ አለው፤ ዳንኤልንም ከጕድጓዱ ያወጡት ዘንድ አዘዘ፤ ዳንኤልም ከጕድጓዱ ወጣ፤ በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጕዳት አልተገኘበትም። 24 ንጉሡም ዳንኤልን የከሰሱ እነዚያን ሰዎች ያመጡአቸው ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱንና ልጆቻቸውንም፥ ሚስቶቻቸውንም በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉአቸው፤ ወደ ጕድጓዱም መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶች ያዙአቸው፤ አጥንታቸውንም ሁሉ ሰባበሩ። 25 ያን ጊዜም ንጉሥ ዳርዮስ በምድር ሁሉ ላይ ወደሚኖሩ ወገኖችና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩም ቋንቋ ወደሚናገሩ ሁሉ ጻፈ፤ እንዲህም አለ፥ “ሰላም ይብዛላችሁ። 26 በመንግሥቴ ግዛት ሁሉ ያሉ ሰዎች በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ አዝዣለሁ፤ እርሱ ሕያው አምላክ ለዘለዓለም የሚኖር ነውና፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፥ ግዛቱም ለዘለዓለም ይኖራል። 27 ያድናል፤ ይታደግማል፤ በሰማይና በምድርም ተአምራትንና ድንቅን ይሠራል፤ ዳንኤልንም ከአንበሶች አፍ አድኖታል።” 28 ይህም ዳንኤል በዳርዮስ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ መንግሥት ከፍ ከፍ አለ። |