ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ትንቢተ ዳንኤል 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የናቡከደነፆር ሁለተኛው ሕልም 1 ከንጉሡ ከናቡከደነፆር፤ በምድር ሁሉ ወደሚቀመጡ ወገኖችና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋንቋም ወደሚናገሩ ሁሉ፥ “ሰላም ይብዛላችሁ። 2 ልዑል አምላክ በፊቴ ያደረገውን ተአምራቱንና ድንቁን እነግራችሁ ዘንድ ወደድሁ። 3 ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘለዓለም መንግሥት ነው፤ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው። 4 “እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር። 5 ሕልም አለምሁ፤ እርስዋም አስፈራችኝ፤ በአልጋዬም ላይ ታወክሁ፤ የራሴም ራእይ አስጨነቀኝ። 6 ስለዚህ የሕልሜን ፍቺ እንዲያስታውቁኝ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ ይገቡ ዘንድ አዘዝሁ። 7 የዚያን ጊዜም የሕልም ተርጓሚዎቹና አስማተኞቹ፥ ከለዳውያኑና ቃላተኞቹ ገቡ፤ ሕልሜንም በፊታቸው ተናገርሁ፤ ፍቺውን ግን አላስታወቁኝም። 8 በመጨረሻም የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፤ እኔም እንዲህ አልሁት፦ 9 የጠቢባን አለቃ ብልጣሶር ሆይ! የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በአንተ ውስጥ እንደ አለ፥ ከምሥጢርም ሁሉ የሚያስቸግርህ እንደሌለ ዐውቄአለሁና ያየሁትን የሕልሜን ራእይ፥ ፍቺውንም ንገረኝ። 10 በአልጋዬ ላይ ራእይ አየሁ፤ እነሆ በምድር መካከል ዛፍ ነበረ፤ ቁመቱም እጅግ ረዥም ነበረ። 11 ዛፉም ትልቅ ሆነ፤ በረታም፤ ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ቅርንጫፉም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ደረሰ። 12 ቅጠሎቹም የተዋቡ ነበሩ፤ ፍሬውም ብዙ ነበረ፤ ሁሉም ከእርሱ ይመገብ ነበረ፤ ከጥላውም በታች የዱር አራዊት ያርፉበት ነበር፥ በቅርንጫፎቹም ውስጥ የሰማይ ወፎች ይቀመጡ ነበር፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከእርሱ ይበላ ነበር። 13 “በአልጋዬም ላይ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ። 14 በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ፦ ዛፉን ቍረጡ፤ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፤ ቅጠሎቹንም አራግፉ፤ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊቱም ከበታቹ፥ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይታወኩ። 15 ነገር ግን ሥሩንና ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፤ በመስክም ውስጥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ፤ እድል ፋንታውም በምድር ሣር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሁን። 16 ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፤ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም ይለፉበት። 17 ልዑል እግዚአብሔር የሰዎችን መንግሥት እንዲገዛ፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው፤ ሰውንም ትዕቢቱ ያዋርደዋል። 18 እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ያለምሁት ሕልም ይህ ነው፤ አንተም ብልጣሶር! ፍቺውን ንገረኝ፤ የመንግሥቴ ጠቢባን ሁሉ ፍቺውን ይነግሩኝ ዘንድ አልቻሉምና፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በአንተ ውስጥ አለና አንተ ትችላለህ።” ዳንኤል የንጉሡን ሕልም እንደ ተረጐመ 19 ያን ጊዜም ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል አንድ ሰዓት ያህል ዐሰበ፤ ልቡም ታወከ። ንጉሡም መልሶ፥ “ብልጣሶር ሆይ! ሕልሙና ፍቺው አያስቸግርህ” አለው። ብልጣሶርም መልሶ አለ፥ “ጌታዬ ሆይ! ሕልሙ ለሚጠሉህ፥ ፍቺውም ለጠላቶችህ ይሁን። 20 ትልቅ የነበረው፥ የበረታውም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ የደረሰው፥ ቅርንጫፉም እስከ ምድር ሁሉ ድረስ የታየው፥ 21 ቅጠሉም አምሮ የነበረው፤ ፍሬውም የበዛው፥ ለሁሉም መብል የነበረበት፥ በበታቹም የምድር አራዊት የተቀመጡ፥ በቅርንጫፎቹም የሰማይ ወፎች ያደሩበት፥ ያየኸው ዛፍ፥ 22 ንጉሥ ሆይ! እርሱ ታላቅና ብርቱ የሆንህ አንተ ነህ፤ ታላቅነትህ በዝቶአል፤ እስከ ሰማይም ደርሶአል፤ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው። 23 ንጉሡም ከሰማይ የወረደውንና፦ ዛፉን ቍረጡ፥ አጥፉትም፤ ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፤ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ በመስክ ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ፥ ሰባት ዘመናትም እስኪያልፉበት ድረስ እድል ፋንታው ከምድር አራዊት ጋር ይሁን ያለውን ቅዱስ ጠባቂ ማየቱ፥ 24 ንጉሥ ሆይ! ፍቺው ይህ ነው፤ በጌታዬ በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው፤ 25 ልዑሉም የሰዎችን መንግሥት እንዲገዛ፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፤ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል። 26 የዛፉንም ጉቶ ተዉት ማለቱ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ እስክታውቅ ድረስ መንግሥትህ ይቈይልሃል። 27 ንጉሥ ሆይ! ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፤ በጽድቅና በምጽዋት ትድናለህ፤ በደልህንና ኀጢአትህንም ለድሆች በመራራት እግዚአብሔር ይቅር ይልሃል።” ሕልሙ እንደ ደረሰ 28 ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ። 29 ከዐሥራ ሁለት ወር በኋላም በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ሲመላለስ፤ 30 ንጉሡ፥ “ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?” ብሎ ተናገረ። 31 ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ መጣና፥ “ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ! መንግሥት ከአንተ ዘንድ ዐለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤ 32 ልዑሉም የሰዎችን መንግሥት እንዲገዛ፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል” አለው። 33 በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕሩም እንደ አንበሳ፥ ጥፍሩም እንደ ንስር እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፤ እንደ በሬም ሣር በላ፤ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። 34 ከእነዚያም ዘመናት በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁ፤ ለዘለዓለም የሚኖረውንም አመሰገንሁ፤ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘለዓለም ግዛት ነውና፥ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና። 35 በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚቃወማት ወይም፥ “ምን ታደርጋለህ?” የሚለው የለም። 36 በዚያን ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፤ ወደ መንግሥቴም ክብር መጣሁ፤ ግርማዬና ውበቴም ወደ እኔ ተመለሰ፤ አማካሪዎችና መኳንንቶችም ፈለጉኝ፤ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፤ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ። 37 አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግነዋለሁ፤ ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ቀና ነውና፤ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና። |