ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ትንቢተ ዳንኤል 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ናቡከደነፆር ያቆመው የወርቅ ምስል 1 ንጉሡ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ቁመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። 2 ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንትንና ሹሞችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዢዎችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፥ ንጉሡ ናቡከደነፆርም ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ። 3 በዚያን ጊዜም መኳንንቱና ሹሞቹ፥ አዛዦቹና አዛውንቶቹ፥ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ፥ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዢዎቹ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ተሰበሰቡ፤ ናቡከደነፆርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ። 4 አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ፥ “ሕዝብና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ! ንጉሥ ይላችኋል፥ 5 የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል ስገዱ፤ 6 ወድቆም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።” 7 ስለዚህ በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ ወገኖችና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ወድቀው፤ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ። ሠለስቱ ደቂቅ 8 በዚያን ጊዜ ከለዳውያን ቀርበው አይሁድን በንጉሡ በናቡከደነፆር ዘንድ ከሰሱ። 9 እንዲህም አሉት፦“ንጉሥ ሆይ፥ ለዘለዓለም ኑር! 10 ንጉሥ ሆይ! የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ሰው ሁሉ ወድቆ ለወርቁ ምስል ይስገድ፥ 11 ወድቆም የማይሰግድ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ብለህ በቃልህ አዘህ ነበር። 12 አሁንም ንጉሥ በባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሾምኻቸው፥ ከአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዝህን እምቢ ያሉ፥ አምላክህን ያላመለኩ፥ ለሠራኸውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ ሚሳቅና ሲድራቅ፥ አብደናጎም የሚባሉ ሦስት ሰዎች አሉ።” 13 ያንጊዜም ናቡከደነፆር ተቈጣ፤ በቍጣም ሲድራቅንና ሚሳቅን፥ አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፤ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። 14 ናቡከደነፆርም፥ “ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? 15 አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?” ብሎ ተናገራቸው። 16 ሲድራቅና ሚሳቅ፥ አብደናጎም መለሱ፤ ንጉሡንም፥ “ናቡከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም። 17 ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፥ ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ 18 ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ፥ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ” አሉት። 19 የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ፥ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፤ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፤ እርሱም ተናገረ፤ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ። 20 ሲድራቅንና ሚሳቅን፥ አብደናጎንም አስረው፥ ወደሚነድድ ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ ኃያላን ሰዎችን አዘዘ። 21 የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ከሰናፊላቸውና ከጫማቸው፥ ከቀሚሳቸውና ከመጎናጸፊያቸውም፥ ከቀረውም ልብሳቸው ጋር አስረው በሚነድድ በእቶን እሳት ውስጥ ጣሉአቸው። 22 የንጉሡም ትእዛዝ እጅግ ስለ በረታ፥ የእቶኑም እሳት እጅግ ስለሚነድድ፥ ሲድራቅንና ሚሳቅን፥ አብደናጎንም የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው። 23 እነዚህም ሦስቱ ሰዎች ሲድራቅና ሚሳቅ፥ አብደናጎም ታስረው በሚነድደው በእቶኑ እሳት መካከል ወደቁ። ጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅ 24 በእሳት መካከልም ተመላለሱ እግዚአብሔርንም ፈጽመው አመሰገኑት። 25 አዛርያም ቁሞ እንዲህ ብሎ ጸለየ፥ በእሳቱም መካከል ምስጋናን ጀመረ፦ 26 “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር፤ ስምህም ለዘለዓለም የተመሰገነና የከበረ ነው። 27 ባመጣህብን ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህና፤ ሥራህ ሁሉ የታመነ ነው፤ ሥርዐትህም ሁሉ የቀና ነው፤ ፍርድህም ሁሉ እውነት ነው። 28 ባደረግህብን ነገር ሁሉ ፍትሕ ርትዕ አደረግህ፤ በእውነተኛ ፍርድህ ስለ ኀጢአታችን ይህን ሁሉ መከራ አምጥተህብናልና በከበረች በአባቶቻችን ሀገር በቅድስት ኢየሩሳሌምም በእውነተኛ ፍርድህ ስለ ኀጢአታችን ይህን ሁሉ መከራ አምጥተህብናልና። 29 የተውንህ እኛ በድለናል፤ ስተናልና በሁሉ በደልን፤ 30 መልካም ይሆንልን ዘንድ፥ እንዳዘዝኸን ሕግህን አልጠበቅንም፤ ትእዛዝህንም አላደረግንም። 31 ያመጣህብንንና ያደረግህብንን ሁሉ በእውነተኛ ፍርድህ አደረግህብን። 32 ከአንተ ፈጽመው በራቁ ኀጢአተኞችና ወንጀለኞች በሚሆኑ በጠላቶቻችን እጅ ጣልኸን፤ ከሰው ሁሉ ዐመፀኛና ክፉ በሆነ ንጉሥም እጅ አሳልፈህ ጣልኸን። 33 አሁንም አፋችንን እንከፍት ዘንድ አገባባችን አይደለም ለሚፈሩህ ለአገልጋዮችህ ኀፍረትና ማሽሟጠጫ ሆነባቸው። 34 ስለ ስምህ ብለህ ፈጽመህ አሳልፈህ አትስጠን። ቃል ኪዳንህንም አትለውጥብን፤ 35 ይቅርታህንም አታርቅብን። ስለ ወዳጅህ ስለ አብርሃም፥ ስለ ባለምዋልህ ስለ ይስሐቅ፤ ስለ ቅዱስህ ስለ እስራኤል። 36 ዘራቸውን እንደ ሰማይ ኮከብ፥ በባሕር ዳር እንደ አለ አሸዋም ታበዛላቸው ዘንድ ስለ ሰጠሃቸው ስለ እነዚህ፥ እነርሱ ከሕዛብ ሁሉ ጥቂቶች ነበሩና። 37 ስለ ኀጢአታችን በሀገሩ ሁሉ ዛሬ የተዋረድን ሆን። 38 በዚህ ወራት አለቃ የለም፤ ነቢይም የለም፤ ንጉሥም የለም፤ ቍርባንም፥ መሥዋዕትም፥ ዕጣንም የሚያጥኑበት የለም፤ ይቅርታህን ያገኙ ዘንድ በፊትህ ፍሬ የሚያፈሩበት ሀገርም የለም። 39 በየዋህ ልቡና በቀና መንፈስ ተቀበልልን እንጂ፤ 40 እንደ ጊደሮችና ላሞች፥ እንደ ሰቡ ብዙ በጎችም መሥዋዕት፤ መሥዋዕታችን ዛሬ በፊትህ እንደዚያ ይሁን። በአንተም ዘንድ ፍጹም ይሁን፤ ያመኑብህ ሁሉ እንዳያፍሩ። 41 አሁንም በፍጹም ልቡናችን እንከተልሃለን፤ እንፈራሃለንም፤ ፊትህንም እንፈልጋለን። 42 አታሳፍረን፤ ነገር ግን እንደ ቸርነትህና እንደ ይቅርታህ ብዛት አድርግልን፥ 43 በተአምራትህም አድነን፤ አቤቱ፥ ለስምህ ምስጋናን ስጥ። 44 አገልጋዮችህን ስቃይ ያሳዩአቸው ሁሉ ይፈሩ፤ በቅሚአቸውም ሁሉ ይፈሩ፤ ኀይላቸውም ይድከም፤ 45 አንተ እግዚአብሔር ብቻህ አምላክ፥ በዓለሙ ሁሉና በሀገሩም ሁሉ የተመሰገንህ እንደ ሆንህ ይወቁ። 46 እነዚያም ብላቴናዎች በንጉሥ ዘንድ ነገር ሠርተው ማጣላታቸውን አልተዉም፤ በእሳቱም ድኝ አደሮማር፥ ቁልቋል፥ ቅንጭብ ጨመሩ። 47 ነበልባሉም ከጕድጓዱ አርባ ዘጠኝ ክንድ ከፍ ከፍ አለ። 48 እሳቱም እየተመላለሰ በከለዳውያን ምድጃ ጕድጓድ አጠገብ ያገኘውን ሁሉ ያቃጥል ነበር። 49 የእግዚአብሔርም መልአክ ከአናንያና ከአዛርያ ከሚሳኤልም ጋር ወደሚነደው ወደ እሳቱ ምድጃ ወርዶ ከምድጃ ያለውን እሳት መታው፤ 50 የእሳቱንም ነበልባል እንደ ቀዝቃዛ ነፋስ አደረገው፤ እነዚያንም ሰዎች እሳቱ ምንም አልነካቸውም፤ የራሳቸውንም ጠጕር አልለበለባቸውም፤ አላስጨነቃቸውምም። 51 ያንጊዜም እነዚያ ሦስቱ ሰዎች ሁሉ በአንድ አፍ ፈጽመው አመሰገኑ፤ በእሳቱ ጕድጓድ ውስጥም እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ እንዲህም አሉ፦ 52 የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍም ያለ ነው። 53 የጌትነቱ ቅዱስ ስምም ይክበር ይመስገን፤ እርሱ የተመሰገነ ነው፤ በዓለሙም ሁሉ ከፍ ከፍ ያለ ነው። 54 በምትመሰገንበት ቅዱስ ቦታ አንተ የከበርህ ነህ፤ አንተ ለዘለዓለም የተመሰገንህና የከበርህ ነህ። 55 በኪሩቤል ላይ ሆነህ ጥልቆችን የምታይ አንተ የከበርህ ነህ፤ አንተ ለዘለዓለም የተመሰገንህ ነህ፤ ከፍ ከፍም ያልህ ነህ። 56 በጌትነትህም ዙፋን አንተ የከበርህ ነህ፤ አንተ ለዘለዓለም የተመሰገንህ ነህ፤ የከበርህም ነህ። 57 ከሰማዮች በላይ የተመሰገንህ ነህ፤ አንተ ለዘለዓለሙ ፈጽመህ የከበርህ ነህ። 58 የጌታ ፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 59 ሰማዮች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፥ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 60 የጌታ መላእክት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 61 ከሰማዮች በላይ ያሉ ውኃዎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 62 የጌታ ኀይላት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 63 ፀሐይና ጨረቃ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 64 የሰማይ ከዋክብት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 65 ጠልና ዝናም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 66 ነፋሳት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 67 እሳትና ዋዕይ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 68 መዓልትና ሌሊት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 69 ጠልና ጤዛ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 70 ብርድና ውርጭ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 71 ብርሃንና ጨለማ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 72 ደጋና ቈላ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 73 በረድና ጕም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 74 መብረቅና ደመና እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 75 ምድር እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 76 ተራሮችና ኮረብቶች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 77 በምድር የሚበቅሉ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 78 ጥልቆች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 79 ባሕርና ፈሳሾች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 80 አንበሪና በውኃ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 81 በሰማይ የሚበርሩ ወፎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 82 አራዊትና እንስሳት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 83 የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 84 እስራኤል እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 85 የጌታ ካህናት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 86 የጌታ ባሪያዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 87 መንፈስና የጻድቃን ነፍሳት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። ‘65’ ጻድቃንና ልባቸው ትሑት የሆኑ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 88 አናንያና አዛርያ፥ ሚሳኤልም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው። 89 እግዚአብሔር ከሞትና ከሲኦል እጅ አድኖናልና፥ ከሚነድድም ከምድጃው እሳት አስጥሎናልና፥ ከነበልባሉም መካከል አውጥቶናልና፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ስሙንም አመስግኑት፤ ቸር ነውና ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና። 90 የአማልክትን አምላክ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁላችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ተገዙለት፤ አመስግኑትም፤ ቸርነቱ ለዘለዓለም ነውና። 91 ንጉሡ ናቡከደነፆርም ሲያመሰግኑ ሰምቶ ተደነቀ፤ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም፥ “ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን?” ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፥ “ንጉሥ ሆይ! እውነት ነው” አሉት። 92 ንጉሡም፥ “እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ፤ ምንም የነካቸው የለም፤ የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል” አለ። 93 የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ፥ “እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ፥ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ” ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅ፥ አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ። 94 አለቆች፥ መሳፍንቱና ሹሞቹም፥ አዛዦቹና የንጉሡ ኃያላን ተሰብስበው እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልበላው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተነካ፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ በላያቸው እንዳልነበረ አዩ። 95 ንጉሡም በፊታቸው ለእግዚአብሔር ሰገደ፥ ናቡከደነፆርም መልሶ እንዲህ አለ፦ መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ፥ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን፥ የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን፥ በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ፥ የአብደናጎም አምላክ ይመስገን። 96 እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ፥ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ይቈረጣሉ፤ ቤታቸውም ይዘረፋል ብየ አዝዣለሁ አለ። 97 የዚያን ጊዜም ንጉሡ፥ ሲድራቅን ሚሳቅንና አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ሾማቸው፤ ከፍ ከፍም አደረጋቸው፤ በግዛቱ ያሉ አይሁድንም ሁሉ አስገዛላቸው። |