ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ትንቢተ ዳንኤል 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የናቡከደነፆር ሕልም 1 ናቡከደነፆርም በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም አለመ፤ መንፈሱም ታወከ፤ ሕልሙንም ዘነጋው። 2 ንጉሡም ሕልሙን እንዲነግሩት የሕልም ተርጓሚዎቹንና አስማተኞቹን፥ መተተኞቹንና ከለዳውያኑንም ይጠሩ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ። 3 ንጉሡም፥ “ሕልም አልሜአለሁ፤ መንፈሴም ታወከብኝ፤ ሕልሜንም ዘነጋሁት” አላቸው። 4 ከለዳውያኑም ንጉሡን በሱርስት ቋንቋ፥ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር፤ ለአገልጋዮችህ ሕልምህን ንገር፤ እኛም ፍቺውን እንነግርሃለን” ብለው ተናገሩት። 5 ንጉሡም መለሰ፤ ከለዳውያኑንም፥ “ነገሩ ከእኔ ዘንድ ርቆአል፤ ሕልሙንና ፍቺውን ባታስታውቁኝ፥ ትገደላላችሁ፤ ቤቶቻችሁም የጉድፍ መጣያ ይደረጋሉ። 6 ሕልሙንና ፍቺውን ግን ብትነግሩኝ፥ ከእኔ ዘንድ ስጦታና ዋጋ፥ ብዙ ክብርም ትቀበላላችሁ፤ ስለዚህም ሕልሙንና ፍቺውን ንገሩኝ” አላቸው። 7 ሁለተኛም ጊዜ መልሰው፥ “ንጉሡ ለአገልጋዮቹ ሕልሙን ይንገር፥ እኛም ፍቺውን እንናገራለን” አሉት። 8 ንጉሡም መልሶ፥ “ነገሩ ከእኔ ዘንድ እንደ ራቀ ታውቃላችሁና ጊዜውን እንደምታስረዝሙ እኔ አውቃለሁ። 9 ሕልሙንም አሁን ባትነግሩኝ አንድ ፍርድ አለባችሁ፥ ጊዜውን ለማሳለፍ የሐሰትንና የተንኰልን ቃል ልትነግሩኝ አዘጋጅታችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ፍቺውንም መናገር እንደምትችሉ አውቃለሁ።” 10 ከለዳውያኑም በንጉሡ ፊት መልሰው፥ “የንጉሡን ነገር ያሳይ ዘንድ የሚችል ሰው በምድር ላይ የለም፤ ታላቅ ንጉሥና አለቃ የሆነ እንደዚያ ያለ ነገር የሕልም ተርጓሚንና አስማተኛን፥ ከለዳዊንም የሚጠይቅ የለም። 11 ንጉሡም የሚጠይቀው ነገር ከባድ ነው፤ መኖሪያቸው ከሥጋ ለባሽ ጋር ካልሆነ ከአማልክት በቀር በንጉሡ ፊት የሚያሳየው ማንም የለም” አሉ። 12 ያንጊዜ ንጉሡ ፈጽሞ ተቈጣ፤ የባቢሎንንም ጠቢባን ሁሉ ያጠፉ ዘንድ አዘዘ። 13 ከንጉሡም ዘንድ ትእዛዝ ወጣ፤ ጠቢባንንም ይገድሉ ዘንድ ጀመሩ፤ ዳንኤልንና ባልንጀሮቹንም ይገድሉአቸው ዘንድ ፈለጉአቸው። 14 የዚያን ጊዜም ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን ይገድል ዘንድ የወጣውን የንጉሡን የዘብ አለቃ አርዮክን በፈሊጥና በማስተዋል ተናገረው፤ 15 የንጉሡ የዘብ አለቃ አርዮክን፥ “ይህ ጭንቅ ትእዛዝ ከንጉሡ ዘንድ ስለ ምን ወጣ?” ብሎ ጠየቀው፤ አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል ነገረው። 16 ዳንኤልም ገብቶ ፍቺውን ለንጉሡ የሚያስታውቅበት ጊዜ ይሰጠው ዘንድ ንጉሡን ለመነ። 17 የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ቤቱ ገባ። ነገሩንም ለባልንጀሮቹ ለአናንያና ለሚሳኤል፥ ለአዛርያም አስታወቃቸው። 18 ዳንኤልና ባልንጀሮቹም ከቀሩት ከባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይሞቱ ስለዚህ ምሥጢር ምሕረትን ከሰማይ አምላክ ለመኑ። 19 የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት። ዳንኤልም የሰማይ አምላክን አመሰገነ። 20 እንዲህም አለ፥ “ጥበብና ምክር፥ ኀይልም ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይመስገን። 21 እሱም ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያስነሣል፤ ነገሥታትንም ይሽራል፤ ጥበብን ለጠቢባን፥ ዕውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል። 22 የጠለቀውንና የተሰወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፤ ብርሃንም ከእርሱ ጋር አለ። 23 አንተ የአባቶቻችን ፈጣሪ! እውቀትንና ጥበብን ሰጥተኸኛልና፥ የለመንሁህንም ነግረኸኛልና፥ የንጉሡን ሕልም፥ ትርጓሜውንም ገልጠህልኛልና እገዛልሃለሁ፤ አመሰግንህምአለሁ።” ዳንኤል ሕልሙን ከነትርጕሙ ለንጉሡ እንደ ነገረ 24 ከዚህም በኋላ ዳንኤል ንጉሡ የባቢሎንን ጠቢባን ያጠፋ ዘንድ ወደ አዘዘው ወደ አርዮክ ገባ፤ “የባቢሎንን ጠቢባን አታጥፋቸው፤ ወደ ንጉሡ አስገባኝ፥ እኔም ሕልሙንና ፍቺውን ለንጉሡ እነግረዋለሁ” አለው 25 የዚያን ጊዜም አርዮክ ዳንኤልን ፈጥኖ ወደ ንጉሡ አስገባውና፥ “ከይሁዳ የምርኮ ልጆች ለንጉሡ ሕልሙንና ፍቺውን የሚነግረውን ሰው አግኝቼአለሁ” አለው። 26 ንጉሡም መለሰ፤ ብልጣሶርም የሚባለውን ዳንኤልን፥ “ያየሁትን ሕልምና ፍቺውንም ትነግረኝ ዘንድ ትችላለህን?” አለው። 27 ዳንኤልም በንጉሡ ፊት እንዲህ ሲል መለሰ፥ “ንጉሥ የሚጠይቀው ይህ ምሥጢር ለአዋቂዎችና ለፈላስፎች፥ ለሟርተኞችና ለጠንቋዮች የሚገለጥ አይደለም።” 28 ነገር ግን ምሥጢርን የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ፤ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ለንጉሡ ለናቡከደነፆር አሳይቶታል። በአልጋህ ላይ የሆነው ሕልምና የራስህ ራእይ ይህ ነው። 29 ንጉሥ ሆይ! ከአንተ በኋላ የሚሆነው ምን እንደ ሆነ በአልጋህ ላይ ታስብ ነበር፤ ምሥጢርንም የሚገልጠው የሚሆነውን ነገር አሳይቶሃል። 30 ነገር ግን ይህ ምሥጢር ለእኔ መገለጡ ፍቺው ለንጉሡ ይታወቅ ዘንድ፥ አንተም የልብህን አሳብ ታውቅ ዘንድ ነው እንጂ በዚህ ዓለም ከአሉ ሰዎች ይልቅ በጥበብ ስለ በለጥሁ አይደለም። 31 “ንጉሥ ሆይ! አንተ አየህ፤ እነሆ ይኸውም አንድ ታላቅ ምስል ነበር፤ እርሱም በፊትህ ቆሞ ነበር፤ መልኩም ግሩም ነበር። 32 የዚህም ምስል ራስ ጥሩ ወርቅ፥ እጆቹ፥ ደረቱና ክንዶቹም ብር፥ ሆዱና ወገቡም ናስ፤ 33 ጭኖቹም ብረት፥ እግሮቹም እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ ነበረ። 34 እጅም ሳይነካው ታላቅ ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች እስከ መጨረሻው ሲመታና ሲፈጭ አየህ። 35 የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ፥ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፤ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንደአለ እብቅ ሆነ፤ ነፋስም ወሰደው፤ ቦታውም አልታወቀም፤ ምስሉንም የመታው ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሁሉ ሞላ። 36 “ሕልምህ ይህ ነው፤ ፍቺውንም በንጉሡ ፊት እናገራለሁ። 37 ንጉሥ ሆይ! የሰማይ አምላክ ጠንካራ መንግሥትን፥ ኀይልንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ። 38 የሰው ልጆች በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ የምድር አራዊትን፥ የሰማይ ወፎችን፥ የባሕር ዓሣዎችንም በእጅህ ሰጥቶሃል፤ ለሁሉም ገዢ አድርጎ ሹሞሃል፤ የወርቁ ራስ አንተ ነህ። 39 ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ እርሱም የብሩ ነው። ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ እርሱም የናሱ ነው። 40 አራተኛውም መንግሥት ሁሉን እንደሚቀጠቅጥና እንደሚያደቅቅ ብረት ይበረታል፤ እነዚህንም ሁሉ እንደሚፈጭ ብረት ይቀጠቅጣል፤ ይፈጭማል። 41 እግሮቹና ጣቶቹም እኩሉ ሸክላ፥ እኩሉም ብረት ሆኖ እንደአየህ፥ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንደ አየኸው፥ የብረት ብርታት ለእርሱ ይሆናል። 42 የእግሮቹም ጣቶች እኩሉ ብረት፥ እኩሉም ሸክላ እንደ ነበሩ፥ እንዲሁ መንግሥቱ እኩሉ ብርቱ፥ እኩሉ ደካማ ይሆናል። 43 ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ እንዲሁ ከሰው ዘር ጋር ይደባለቃሉ፤ ነገር ግን ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ እንዲሁ እርስ በርሳቸው አይጣበቁም 44 በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘለዓለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ድል ታደርጋቸዋለች፤ ታጠፋቸውማለች፤ ለዘለዓለምም ትቆማለች። 45 ድንጋዩም እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ ብረቱንና ናሱን፥ ሸክላውንና ብሩን፥ ወርቁንም ሲፈጨው እንደ አየህ፥ እንዲሁ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ታላቁ አምላክ ለንጉሡ አሳይቶታል፤ ሕልሙም እውነተኛ፥ ፍቺውም የታመነ ነው።” ንጉሡ፥ ዳንኤልን እንደ አከበረው 46 የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር በግምባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት። ፈጽሞም አከበረው፥ ገጸ በረከትም ሰጠው፤ መልካም መዓዛም ያቀርቡለት ዘንድ አዘዘ። 47 ንጉሡም ዳንኤልን፥ “ይህን ምሥጢር ትገልጥ ዘንድ ተችሎሃልና በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ጌታ፥ ምሥጢርም ገላጭ ነው” ብሎ ተናገረው። 48 ንጉሡም ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ብዙም ታላቅ ስጦታ ሰጠው፤ በባቢሎንም አውራጃዎች ሁሉ ላይ ሾመው፤ በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ ዋነኛ አለቃ አደረገው። 49 ዳንኤልም ንጉሡን ለመነ፤ እርሱም ሲድራቅንና ሚሳቅን፥ አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን በንጉሡ አደባባይ ነበረ። |