ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ትንቢተ ዳንኤል 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “እኔም በሜዶናዊው በዳርዮስ መጀመሪያ ዓመት አጸናውና አበረታው ዘንድ ቆሜ ነበር። 2 “አሁንም እውነትን እነግርሃለሁ። እነሆ ሦስት ነገሥታት ደግሞ በፋርስ ይነሣሉ፤ አራተኛውም ከሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጸጋ ይሆናል፤ በባለጸግነቱም በበረታ ጊዜ በግሪክ መንግሥት ላይ ሁሉን ያስነሣል። 3 ኀያልም ንጉሥ ይነሣል፤ ትልቅ አገዛዝንም ይገዛል፤ እንደ ፈቃዱም ያደርጋል። 4 በተነሣም ጊዜ መንግሥቱ ትሰበራለች፤ በአራቱም ነፋሳት ትበተናለች፤ ለዘሩ ግን አይከፋፈልም፤ ከእርሱም በኋላ እርሱ እንደ ገዛበት አገዛዝ አይሆንም፤ መንግሥቱ ታልፋለች፤ ከእነዚህም ለሌሎች ትሰጣለች። 5 “የአዜብም ንጉሥ ይበረታል፤ ከአለቆቹም አንዱ በእርሱ ላይ ይበረታል፤ ከእርሱም ይልቅ ብዙ ግዛትን ይገዛል። 6 ከዘመናትም በኋላ ይቀላቀላሉ፤ የአዜብም ንጉሥ ሴት ልጅ ቃል ኪዳን ለማድረግ ወደ መስዕ ንጉሥ ትመጣለች። የክንድዋ ኀይል ግን አይጸናም፤ ዘሩም አይጸናም፤ እርስዋና እርስዋን ያመጡ፥ የወለዳትም፥ በዚያም ዘመን ያጸናት አልፈው ይሰጣሉ። 7 ነገር ግን ከሥርዋ ቍጥቋጥ አንዱ በስፍራው ይነሣል፤ ወደ ሠራዊቱም ይመጣል፤ ወደ መስዕም ንጉሥ አምባ ይገባል፤ በላያቸውም ያደርጋል፤ ያሸንፍማል። 8 አማልክቶቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎቻቸውን ከብርና ከወርቅም የተሠሩትን የከበሩትን ዕቃዎች ወደ ግብፅ ይማርካል፤ እርሱም ከመስዕ ንጉሥ በላይ ሆኖ ይቆማል። 9 ይህም ወደ አዜብ ንጉሥ መንግሥት ይገባል፥ ነገር ግን ወደ ገዛ ምድሩ ይመለሳል። 10 “ልጆቹም ይዋጋሉ፤ ብዙ ሕዝብንና ሠራዊትን ይሰበስባሉ፤ እርሱም ይመጣል፤ ይበረታማል፤ ያልፍማል፤ ተመልሶም እስከ አምባው ድረስ ይዋጋል። 11 የአዜብም ንጉሥ ይቈጣል፤ ወጥቶም ከመስዕ ንጉሥ ጋር ይዋጋል፤ ብዙ ሕዝብንም ለሰልፍ ያቆማል፤ ሕዝቡም አልፎ በእጁ ይሰጣል። 12 ሕዝቡንም ይወስዳል፤ ልቡንም ያስታብያል፤ አእላፋትንም ይጥላል፤ ነገር ግን አያሸንፍም። 13 የመስዕም ንጉሥ ይመለሳል፥ ከቀደመውም የበለጠ ብዙ ሕዝብን ያቆማል፤ በዘመናትና በዓመታትም ፍጻሜ ከታላቅ ሠራዊትና ከብዙ ሀብት ጋር ይመጣል። 14 በዚያም ዘመን ብዙ ሰዎች በአዜብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፤ ከሕዝብህም መካከል የዐመፅ ልጆች ራእዩን ያጸኑ ዘንድ ይነሣሉ፤ ነገር ግን ይወድቃሉ። 15 የመስዕም ንጉሥ ይመጣል፤ አፈርንም ይደለድላል፤ የተመሸገችንም ከተማ ይይዛል፤ የአዜብም ክንድ የተመረጡትም ሕዝብ አይቆሙም፤ ለመቋቋምም ኀይል የላቸውም። 16 ወደ እርሱ የሚመጣው እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ በፊቱም የሚቆም የለም፤ በመልካሚቱም ምድር ይቆማል፤ ሁሉም በእጁ ይፈጸማል። 17 ከመንግሥቱም ሁሉ ኀይል ጋር ይመጣ ዘንድ ፊቱን ያቀናል፤ ከእርሱም ጋር አንድነትን ያደርጋል፤ ለጥፋቱም ሴት ልጅ ትሰጠዋለች፤ እርስዋም አትጸናም፤ ለእርሱም አትሆንም። 18 ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ደሴቶች ይመልሳል፤ ብዙዎችንም ይወስዳል፤ የኀፍረት አለቆቹንም ይሽራል፤ ኀፍረቱም በላዩ ይመለሳል። 19 ፊቱንም ወደ ገዛ ምድሩ አንባዎች ይመልሳል፤ ደክሞም ይወድቃል፤ አይገኝምም። 20 “የመንግሥትን ሥልጣንና ክብር የሚሽር ይነሣል፤ በመንበሩም ይቀመጣል፤ ነገር ግን በቍጣም ሳይሆን፥ በጦርነትም ሳይሆን ከጥቂት ቀን በኋላ ይሰበራል። ጨካኙ የሶርያ ንጉሥ 21 በእርሱም ስፍራ የተጠቃ ሰው ይነሣል፤ የመንግሥቱንም ክብር አይሰጡትም፤ በቀስታ ይመጣል፤ መንግሥትንም በማታለል ይይዛል። 22 የሚጐርፉ ተዋጊዎቹም ክንዶች ከፊቱ ይሰበራሉ፤ እርሱና የቃል ኪዳኑ አለቃም ይሰበራሉ። 23 ከእርሱም ጋር ከተወዳጀ በኋላ ተንኰልን ያደርጋል፤ ከጥቂትም ሕዝብ ጋር ወጥቶ ይበረታል። 24 በቀስታም ከሀገር ሁሉ ወደ ለመለመችው ክፍል ይገባል፤ አባቶቹና የአባቶቹ አባቶች ያላደረጉትንም ያደርጋል፤ ብዝበዛውንና ምርኮውን፥ ሀብቱንም በመካከላቸው ይበትናል፤ በምሽጎችም ላይ እስከ ጊዜው ድረስ ዐሳቡን ይፈጥራል። 25 በታላቅም ሠራዊት ሆኖ ኀይሉንና ልቡን በአዜብ ንጉሥ ላይ ያስነሣል፤ የአዜብም ንጉሥ በታላቅና በብዙ ሠራዊት ይበረታል፤ ነገር ግን ዐሳብ በእርሱ ላይ ይፈጥራሉና አይጸናም። 26 መብሉንም የሚበሉ ሰዎች ይሰብሩታል፤ ሠራዊቱም ይጐርፋል፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ። 27 እነዚህም ሁለት ነገሥታት በልባቸው ክፋትን ያደርጋሉ፤ በአንድ ገበታም ተቀምጠው ሐሰትን ይናገራሉ፤ ገና ጊዜው አልደረሰምና አይከናወንላቸውም። 28 “ከብዙም ሀብት ጋር ወደ ምድሩ ይመለሳል፥ ልቡም በተቀደሰው ቃል ኪዳን ላይ ይሆናል፤ ፈቃዱንም ያደርጋል፥ ወደ ገዛ ምድሩም ይመለሳል። 29 በተወሰነውም ጊዜ ይመለሳል፤ ወደ አዜብም ይመጣል፤ ነገር ግን የኋለኛው እንደ ፊተኛው አይሆንም። 30 ጺም፥ ከይተምና ኔባእ በእርሱ ላይ ይመጣሉ ስለዚህ አዝኖ ይመለሳል፥ በቅዱሱም ቃል ኪዳን ላይ ይቈጣል፤ ፈቃዱንም ያደርጋል፤ ተመልሶም ቅዱሱን ቃል ኪዳን የተዉትን ሰዎች ይመለከታል። 31 ዘሮችም ከእርሱ ይነሣሉ፤ ቤተ መቅደሱንም ያረክሳሉ፤ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፤ የጥፋትንም ርኵሰት ያቆማሉ። 32 ቃል ኪዳኑን የሚበድሉትንም በማታለል ያስታሉ፤ ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ፤ ያደርጋሉም። 33 በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥበበኞች ብዙ ሰዎችን ያስተምራሉ፤ ነገር ግን በሰይፍና በእሳት ነበልባል በምርኮና በብዙ ዘመን ብዝበዛ ይደክማሉ። 34 በመከራም ጊዜ በጥቂት ርዳታ ይረዳሉ፤ ብዙ ሰዎችም በግብዝነት ወደ እነርሱ ይጨመራሉ። 35 ጊዜው ገና አልደረሰምና ያግሏቸው፥ ያነጿቸውና ያጠሯቸው ዘንድ ከዐዋቂዎች እኩሌቶቹ እስከ ጊዜው ድረስ መከራ ይቀበላሉ፤ በከበረ ቦታ የሚቆም፥ መጽሐፍንም የሚያነብብ ሰው ይህን ነገር ልብ ያድርግ። 36 “ንጉሡም እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ ራሱንም ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ በአማልክት ሁሉ ላይ ራሱን ታላቅ ያደርጋል፤ በአማልክትም አምላክ ላይ በትዕቢት ይናገራል፤ ቍጣም እስኪፈጸም ድረስ ይከናወንለታል፤ የተወሰነው ይደረጋልና። 37 የአባቶቹንም አምላክ፥ የሴቶችንም ምኞት አያከብርም፤ ራሱንም በሁሉ ላይ ታላቅ ያደርጋልና አማልክትን ሁሉ አያውቅም። 38 ጽኑዕ በሆነ በእግዚአብሔር ሥልጣንም ይኰራል፤ አባቶቹም ያላወቁትን አምላክ በወርቅና በብር፥ በዕንቍና በከበረ ነገር ያከብረዋል። 39 ከባዕድም አምላክ ጋር የተመሸጉ ጽኑ አምባዎችን ያደርጋል፤ ክብርን ያበዛላቸዋል፤ በብዙም ላይ ያስገዛቸዋል፤ ምድርንም በዋጋ ይከፍላል። 40 “በፍጻሜ ዘመንም የዐዜብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል፤ የመስዕም ንጉሥ ከሠረገሎችና ከፈረሰኞች፥ ከብዙ መርከቦችም ጋር ይመጣበታል፤ ወደ ሀገሮችም ይገባል፤ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል። 41 ወደ መልካሚቱም ምድር ይገባል፤ ብዙ ሀገሮችም ይወድቃሉ፤ ነገር ግን ኤዶምያስና ሞዓብ፥ ከአሞንም ልጆች የበለጡት ከእጁ ይድናሉ። 42 እጁን በሀገሮች ላይ ይዘረጋል፤ የግብፅም ምድር ከእጁ አታመልጥም። 43 በወርቅና በብርም መዝገብ ላይ ፥ በከበረችም በግብፅ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሠለጥናል፤ የሊብያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ረዳቶች ይሆኑታል። 44 ከምሥራቅና ከሰሜን ግን ወሬ ይደርሰዋል፤ ይቸኩላልም፤ ብዙ ሰዎችንም ይገድልና ፈጽሞ ያጠፋ ዘንድ በታላቅ ቍጣ ይወጣል። 45 ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና በከበረው በቅዱሱ ተራራ መካከል ይተክላል፤ እስከ ጊዜውም ይበረታል። የሚረዳውም የለም። |