ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ ትንቢተ ዳንኤል 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳንኤል በጤግሮስ ወንዝ አጠገብ ያየው ራእይ 1 በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመተ መንግሥት ብልጣሶር ለተባለው ለዳንኤል ነገር ተገለጠለት፤ ነገሩም እውነት ነበረ፤ ታላቅ ኀይልና ማስተዋልም በራእዩ ውስጥ ተሰጠው። 2 በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። 3 ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፤ ሥጋና የወይን ጠጅም በአፌ አልገባም፤ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። 4 ከመጀመሪያውም ወር በሃያ አራተኛው ቀን ጤግሮስ በተባለው በታላቁ ወንዝ አጠገብ ነበርሁ። 5 ዐይኖችንም አነሣሁ፤ እነሆም በፍታ የለበሰውንም ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ። 6 አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ። 7 እኔም ዳንኤል ብቻዬን ራእዩን አየሁ፤ ከእኔ ጋር የነበሩ ሰዎች ግን ራእዩን አላዩም፤ ነገር ግን ታላቅ ድንጋጼ ወደቀባቸው፤ ከፍርሃትም የተነሣ ሸሹ። 8 እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኀይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ፤ ኀይልም አጣሁ። 9 የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ። 10 እነሆም እጅ ዳሰሰችኝ፤ እጄንም ይዞ በጕልበቴ አቆመኝ። 11 እርሱም፥ “እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ! እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፤ ቀጥ ብለህም ቁም” አለኝ። ይህንም ቃል በአለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ። 12 እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ዳንኤል ሆይ! አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ከአደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። 13 የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን በፊቴ ቁሞ ነበር። እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም ከፋርስ ንጉሥ ጋር በዚያ ተውሁት። 14 የራእዩም ጊዜ ገና ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።” 15 ይህንም ቃል በተናገረኝ ጊዜ ፊቴን ወደ ምድር ደፋሁ፤ ዲዳም ሆንሁ። 16 እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሬን ዳሰሰኝ፤ ያን ጊዜም አፌን ከፍቼ ተናገርሁ፤ በፊቴም ቁሞ የነበረውን፥ “ጌታዬ ሆይ! ከራእዩ የተነሣ ሰውነቴ ታወከች፤ ኀይልም አጣሁ። 17 አቤቱ! አገልጋይህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ እንዴት ይችላል? ከአሁንም ጀምሮ ኀይሌ አይጸናም፤ እስትንፋስም አልቀረልኝም” አልሁት። 18 ደግሞ ሰው የሚመስል ዳሰሰኝ፤ አበረታኝም። 19 እርሱም፥ “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ! አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፤ ጽና፥” አለኝ። በተናገረኝም ጊዜ በረታሁና፥ “አበርትተኸኛልና ጌታዬ ይናገር” አልሁ። 20 እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ወደ አንተ የመጣሁት ስለ ምን እንደ ሆነ፥ ታውቃለህን? አሁንም የፋርስን አለቃ እወጋው ዘንድ እመለሳለሁ፤ እኔም ስወጣ፥ እነሆ የግሪኮች አለቃ ይመጣል። 21 ነገር ግን በእውነት መጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም። |