ሐዋርያት ሥራ 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር እንደ ተገናኘ 1 ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ ሄደ። 2 አቂላ የሚባል አንድ አይሁዳዊም አገኘ፤ የትውልድ ሀገሩም ጳንጦስ ነው፤ እርሱም ከጥቂት ወራት በፊት ከኢጣልያ ተሰዶ መጣ፤ ሚስቱ ጵርስቅላም አብራው ነበረች፤ ቀላውዴዎስ አይሁድ ከሮም እንዲሰደዱ አዝዞ ነበርና ወደ እነርሱ መጣ። 3 ሥራቸው አንድ ስለ ነበረ ድንኳን ሰፊዎችም ስለ ነበሩ ከእነርሱ ጋር አብሮ ኖረ፤ በአንድነትም ይሠሩ ነበር። 4 ጳውሎስም በየሰንበቱ በምኵራብ ይከራከራቸው ነበር፤ አይሁድንና አረማውያንንም ያሳምናቸው ነበር። 5 ሲላስና ጢሞቴዎስም ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ ጳውሎስ፥ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ቃሉን በማስተማር ይተጋ ነበር። 6 እነርሱም በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ ልብሱን አራግፎ፥ “እንግዲህ እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ነው፤ ከእንግዲህስ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው። 7 ከዚያም አልፎ ስሙ ኢዮስጦስ ወደሚባል እግዚአብሔርን ወደሚፈራ ሰው ቤት ገባ፤ ቤቱም በምኵራብ አጠገብ ነበር። 8 የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከነቤተ ሰቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመነ፤ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙዎች ሰምተው አምነው ተጠመቁ። 9 ጌታችንም ጳውሎስን በሌሊት ራእይ እንዲህ አለው፥ “አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር፥ ዝምም አትበል፤ 10 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ማንም ሊጐዳህ የሚነሣብህ የለም፤ በዚች ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና።” 11 ጳውሎስም የእግዚአብሔርን ቃል እየአስተማራቸው ዓመት ከስድስት ወር በቆሮንቶስ ተቀመጠ። 12 ጋልዮስም የአካይያ አገረ ገዢ በሆነ ጊዜ አይሁድ ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ወደ ሸንጎም አመጡት። 13 እንዲህም አሉት፥ “ይህ ሰው ኦሪትን በመቃወም እግዚአብሔርን ያመልኩ ዘንድ ሰዎችን ያባብላል።” 14 ጳውሎስም ይመልስላቸው ዘንድ አፉን ሊከፍት ወድዶ ሳለ አገረ ገዢው ጋልዮስ መልሶ አይሁድን እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ አይሁድ ሆይ፥ የበደላችሁ በደል ቢኖር፥ ወይም ሌላ በደል ቢኖርበት አቤቱታችሁን በሰማሁና ባከራከርኋችሁ ነበር። 15 ስለ ትምህርትና ስለ ስሞች፥ ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን ለራሳችሁ ዕወቁ፤ እኔ እንዲህ ያለ ነገር ልሰማ አልፈቅድም።” 16 ከሸንጎውም አባረራቸው። 17 አረማውያንም ሁሉ የምኵራቡን አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በሸንጎ ፊት ደበደቡት፤ የእርሱም ነገር ጋልዮስን ምንም አላሳዘነውም። 18 ጳውሎስም እንደ ገና በወንድሞቹ ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጠ፤ በሰላምም ሸኙትና ወደ ሶርያ በባሕር ተጓዘ፤ ጵርስቅላና አቂላም አብረውት ነበሩ፤ ስእለትም ነበረበትና በክንክራኦስ ራሱን ተላጨ። 19 ወደ ኤፌሶንም ደረሱ፤ በዚያም ተዋቸውና እርሱ ብቻውን ወደ ምኵራብ ገብቶ አይሁድን ተከራከራቸው። 20 እነርሱም ብዙ ጊዜ እንዲሰነብት ማለዱት፤ ነገር ግን አልወደደም። 21 ከዚህም በኋላ በሚሸኙት ጊዜ፥ “እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንደገና እመለሳለሁ፤ አሁን ግን የሚመጣውን በዓል በኢየሩሳሌም ላደርግ እወዳለሁ” አላቸው፤ ከኤፌሶንም በመርከብ ሄደ። 22 ወደ ቂሳርያም ደረሰ፤ ከዚያም ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ሄደ። 23 ጥቂት ቀንም ተቀመጠ፤ ከዚያም ወጥቶ በገላትያና በፍርግያ በኩል በተራ እየዞረ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም አጸናቸው። 24 በእስክንድርያም የሚኖር፥ ንግግር የሚችልና መጽሐፍን የሚያውቅ አጵሎስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን መጣ። 25 እርሱም የእግዚአብሔርን መንገድ የተማረ ነበር፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም ሊያስተምርና ሊመሰክር ከልቡ የሚተጋ ነበር፤ ነገር ግን የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ተጠምቆ ነበር። 26 እርሱም በምኵራብ በግልጥ ይናገር ጀመር፤ ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ ወደ ማደሪያቸው ወስደው ፍጹም የእግዚአብሔርን መንገድ አስረዱት። 27 ወደ አካይያም ሊሄድ በወደደ ጊዜ ወንድሞች አጽናኑት፤ እንዲቀበሉትም ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ ወደ እነርሱም በደረሰ ጊዜ፥ በእግዚአብሔር ጸጋ ላመኑት ብዙ አስተማራቸው፤ ትልቅ ርዳታም ረዳቸው። 28 ተሰብስበው ሳሉም በሕዝቡ ሁሉ ፊት አይሁድን በግልጥ እጅግ ይከራከራቸው ነበር፤ ስለ ኢየሱስም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት ማስረጃ ያመጣላቸው ነበር። |