ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ጌታውም አዳምን ይቤዠው ዘንድ አለው፤ አንተንም ያሳፍርሃል፤ በጉንም ከተኵላ አፍ ያድነዋል። 2 ነገር ግን አንተ የገዛሃቸውን ሰዎች ከአንተ ጋር ይዘህ ወደ ጥፋት ትሄዳለህ። 3 የፈጣሪያቸው የእግዚአብሔርን ሕግ የጠበቁ ግን የእርሱ እድል ፋንታ ያደርጋቸው ዘንድ፥ የፈጣሪያቸው የእግዚአብሔርንም ሕግ እንዳንተ ካልተላለፉ ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ያመሰግኑት ዘንድ ከክፉ ሥራህ ከሰወራቸው ከፈጣሪያቸው ከእግዚአብሔር ጋር ደስ ይላቸዋል። 4 አንተ ግን ከመላእክቱ ጋራ ታመሰግነው ዘንድ እንደ አንተ ካሉት ሁሉ ይልቅ መርጦ የሰጠህ እግዚአብሔር በትዕቢትህ ከፍ ያለ ዙፋንን ነሳህ። 5 አንተም ታበይህ፤ ዲያብሎስም ተባልህ፤ ሠራዊቶችህም አጋንንት ተባሉ። 6 እግዚአብሔርን የሚወዱ ግን እንደ ቅዱሳን መላእክት ለእርሱ ወገኖቹ ይሆናሉ፤ የሚያመሰግኑት ሱራፌልና ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘርግተው ያለማቋረጥ ያመሰግናሉ። 7 አንተ ግን በመልክህ ከተፈጠሩ ከነገድህና ከሠራዊትህ ጋር ሁልጊዜ ታመሰግነው ዘንድ ምስጋናህን በትዕቢትህና በስንፍናህ አጠፋህ። 8 እንደ አንተ ያለ መፍጠር የማይቻለው መስሎህ አንተ የፈጠረህ የእግዚአብሔርን ምስጋና በዘነጋህ ጊዜ፥ ዐሥረኛ ነገድ አድርጎ የፈጠረህ የእግዚአብሔር ምስጋናው እንዳይጐድል አንተም ከወንድሞችህ አንድነት በተለየህ ጊዜ የፈጠረህ የእግዚአብሔር ምስጋናው እንዳይጐድል፥ 9 አንተም በልቡናህ ትዕቢት የፈጠረህ የእግዚአብሔርን ምስጋና ቸል ባልህ ጊዜ፥ እርሱም በተቈጣህና፤ በተዘባበተብህ ጊዜ፤ ከሠራዊቶችህም ጋራ በገሃነም እንቅጥቅጥ በአጋዘህ ጊዜ 10 በቅዱሳት እጆቹ ከምድር መሬትን ወሰደ፤ ውኃንና እሳትን፥ ነፋስንም ጨመረ፤ አዳምንም በመልኩና በምሳሌው ፈጠረው። 11 ምስጋናው በአንተ ጉድለት ይመላ ዘንድ በእጁ በፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ላይ ሾመው። የመሬታዊውም ምስጋና ከሰማያውያኑ ምስጋና ጋር ተጨመረ፤ ምስጋናቸውም እኩል ሆነ። 12 አንተ ግን በትዕቢትህና በአንገትህ መደንደን ተሰደድህ፤ ከፈጠረህ ከእግዚአብሔርም ጌትነት ወጥተህ ራስህን አጠፋህ። 13 የእግዚአብሔርነቱ ምስጋና እንዳይጐድል እግዚአብሔር በፈቃዱ ምክር የሚያመሰግነውን ፈጥሯልና ምስጋናው እንዳይጐድል ዕወቅ። 14 እርሱ ሳይደረግ ሁሉን ያውቃልና፥ ትእዛዙንም እንደምታፈርስ ሳይፈጥርህ ዐወቀህ፤ ዓለም ሳይፈጠር በእርሱ ዘንድ የተሰወረ ምክር ነበረና በካድኸው ጊዜ ባርያው አዳምን በመልኩና በምሳሌው ፈጠረው። 15 ሰሎሞን፥ “ከኮረብቶች በፊት ወለደኝ፤ ዓለምም ሳይከናወን የምድርም መሠረት ሳይመሠረት፥ 16 የተራራዎችና የኮረብቶች መቋምያ ሳይተከል፥ የዓለምም ጐዳና ሳይጸና፥ የፀሐይና የጨረቃ ብርሃን ሳይበራ፥ የከዋክብትና የዘመኖች ምግብና ሳይታወቅ፥ 17 ሌሊትና መዓልት ሳይፈራረቁ፥ ባሕርም ባሸዋ ሳትወሰን፥ የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ሳይፈጠር፥ 18 ዛሬም የሚታየው ሁሉ ሳይታይ፥ ዛሬ የሚጠራው ስም ሁሉ ሳይጠራ ፈጠረኝ” ብሎ እንደ ተናገረ፥ አንተና እንዳንተ ያሉ መላእክት፥ ባርያው አዳምም በእግዚአብሔር ኅሊና ውስጥ ነበራችሁ። 19 አንተ በካድህ ጊዜ ቅዱስ ስሙ ይመሰገን ዘንድ፥ አንተም በታበይህ ጊዜ ከመሬት በፈጠረው በተዋረደ በባርያው በአዳም ይመሰገን ዘንድ አዳምን ፈጠረው። 20 እግዚአብሔር የድሆችን ጸሎት ከሩቅ ይሰማልና፥ የተዋረዱ ሰዎችንም ምስጋና እግዚአብሔር ይወዳልና። 21 እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ነገር ቸል ይላል፥ የፈረስን ኀይል አይወድምና፥ በሰው ጕልበትም ደስ አይለውምና። 22 ነገር ግን እግዚአብሔር በሚፈሩትና ስለ ኀጢአታቸው ጩኸው በሚያለቅሱ ደስ ይለዋል። 23 አንተ በንስሓ መናዘዝ ተሳነህ። 24 ያ መሬት ግን ስለ ኀጢአቱ በእግዚአብሔር ፊት ፈጽሞ እያለቀሰ በንስሓ ተመለሰ። 25 አንተስ በልብህ ትዕቢትና በአንገትህ መደንደን የሰላም መንገድን አላወቅሃትም፥ ንስሓንም አላወቅሃትም፥ በንስሓ፥ በልቅሶና በእንባ በፈጣሪህ በእግዚአብሔር ፊት መናዘዝ ተሳነህ። 26 ያ አመድና መሬት የሆነ ድሃ ግን በልቅሶና በእንባ ወደ ንስሓ፥ ወደ ሰላምና ወደ ትሕትና መንገድ ተመለሰ። 27 አንተስ ለፈጠረህ ለእግዚአብሔር ራስህንና የልብህን ቀፈት አላዋረድህም። 28 እርሱ ግን በበደለው በደል ራሱን አዋርዶ ተናዘዘ፤ አልታበየምም። 29 ያንም ስሕተት የፈጠረው እርሱ አይደለም። ከአንተ የተገኘ ነው እንጂ፥ ወንጀልን ፈጥረህ አውጥተኸዋልና። በትዕቢትህም ከአንተ ጋራ ወደ አንተ ጥፋት ወሰድኸው። 30 ሁለታችሁን ሁሉ ሳይፈጥራችሁ ዐውቋችኋልና፥ አካሄዳችሁንም ዐውቋልና ይህ የተደረገ በልብህ ትዕቢት እንደ ሆነ እርሱ ያውቃል። 31 ያን የትዕቢት ተንኰል የሌለውን ግን በንስሓ፥ በልቅሶና በእንባ መለሰው። 32 አንተ ግን በልብህ ትዕቢት በንስሓ መናዘዝ ተሳነህ። በድሎ በንስሓ የማይናዘዝ ሰው ከቀድሞ በደሉ ይልቅ በደሉን ያከፋልና። 33 ነገር ግን በድሎ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፊት የሚናዘዝና የሚያለቅስ፥ እርሱ በእውነት ንስሓ ገባ፤ የጌታውንም ልብ ያራራ ዘንድ የመዳኑን መንገድ አገኘ፤ በጌታውም ፊት ተናዘዘ፤ ጌታውም በባሪያው ላይ ይቈጣ ዘንድ ቀድሞ ከመከረበት ያቃልልለታል፤ በብዙ ንስሓና ስግደት ተናዝዞአልና። የቀደመ ኀጢአቱንም ይቅር ይለዋል። 34 ወደ ቀደመ በደሉም ካልተመለሰ፥ ይህንም ካደረገ ይህ ፍጹም ንስሓ ነው። አዳምስ ፈጣሪውን ማሰብንና ለፈጣሪው መናዘዝን አልዘነጋም። 35 አንተም ለፈጣሪህ በንስሓ ተናዘዝ፤ በእርሱ ላይና በእጁ ሥራ ላይም በደልን አታብዛ፤ እነርሱ ሥጋውያንና ደማውያን ስለ ሆኑ የፈጠራቸው እግዚአብሔር ድካማቸውን ያውቃልና። 36 ነፍሳቸውም ከተለየች በኋላ ሥጋቸው እግዚአብሔር እስከፈቀዳት ቀን ድረስ ትቢያ ይሆናል። |