ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ለአንተስ ፈጣሪህ ወደላከህ እየተላክህ ፈጽመህ ታመሰግን ዘንድ አንድ አሳብን ፈጠረልህ። 2 ለአዳም ግን ክፉ የሆኑ አምስት አሳቦችና በጎ የሆኑ አምስት አሳቦች ዐሥር አሳቦች ተሰጡት። 3 ዳግመኛም እንደ ባሕር ሞገድ፥ ከምድርም አንሥቶ ትቢያን እንደሚበትን ጥቅል ነፋስ፥ ነፋስም እንደሚያናውጠው እንደ ባሕር ሞገድ የሚታወኩ ብዙ አሳቦች አሉት፤ እንደማይቈጠር እንደ ዝናብም ጠብታ በልቡ ከአለ ከማይቈጠር ከአሳቡ ብዛት የተነሣ የአዳም አሳብ እንደዚሁ ነው። 4 የአንተ ግን አሳብህ አንዲት ናት፤ ሥጋዊ አይደለህምና ሌላ አሳብ የለህም። 5 አንተ ግን በእባብ ልቡና አድረህ አንድ አካል የሆነ አዳምን በክፉ ሽንገላ አጠፋኸው፤ ሔዋንም የእባብን ነገር ሰማች፤ ሰምታም እንዳዘዘቻት አደረገች። 6 መጥታም የእግዚአብሔር መጀመሪያ ፍጥረቱ አዳምን የበለስን ፍሬ በማብላት አሳተችው፤ የፈጣሪዋንም ትእዛዝ ስለ ተላለፈች በእርስዋና በልጆችዋ ሞትን አመጣች። 7 በእግዚአብሔርም እውነተኛ ፍርድ ከገነት ወጡ፤ ተጣልቶም ከገነት አላራቃቸውም። ነገር ግን በተሰደዱበት ምድር በሆዳቸው ፍሬ በልጆቻቸውና በምድራቸው ፍሬ አረጋጋቸው። 8 በቅንአትህም ከገነት ባስወጣሃቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከገነት የለመለሙ ዕፀዋትን ሰጣቸው፤ ይተክሉ ዘንድ እግዚአብሔር በሰጣቸው በገነት ፍሬና በምድር ፍሬ ይረጋጉ ዘንድ፤ 9 ልጆችን በማየት፥ ገነትንና ምድር ከአፈር ያበቀለችውን የምድር ፍሬ በማየት ልቡናቸውን እጅግ ደስ ያሰኙ ዘንድ፤ እርሱንም በበሉ ጊዜ ከገነት እነርሱን ካስወጣህበት ኀዘን ፈጽመው ይረጋጋሉ። 10 እግዚአብሔርም ፍጥረቱን ማረጋጋት ያውቃልና በልጆቻቸውና በምድር ፍሬ ልቡናቸው ይረጋጋል። 11 ወደዚች የእሾህና የአሜከላ ምድርም ተሰደዋልና ልቡናቸውን በእህልና በውኃ ያጸናሉ። |