ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “አንተ ግን እንደ ባርያዬ እንደ ኢዮብ ማሳት የተሳነህን እኔ በክብር የአንተን ዙፋን አወርሳቸዋለሁ፤ አንተ ማሳት ለተሳነህ ሰዎች መንግሥተ ሰማያትን እሰጣቸዋለሁ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር።” 2 እኔም የአዳምን ልጆች በሁሉ እተነኰልባቸዋለሁ፤ እነርሱን ማሳት ከተቻለኝ በበጎ ሥራ ይጸኑ ዘንድ አልተዋቸውም፤ የአዳምን ልጆች ሁሉ እተነኰልባቸዋለሁና፥ የዓለምን ምኞትም አጣፍጥላቸዋለሁና። 3 መብልን በመውደድ፥ መጠጥንም በመውደድ፥ ልብስን በመውደድም ቢሆን፥ ነገርንም በመውደድ፥ በመስጠትም በመንሣትም ቢሆን፥ 4 መስማትንና ማየትንም በመውደድ ቢሆን፥ መዳሰስንና መሄድንም በመውደድ ቢሆን፥ ትዕቢትንና ነገርንም በማብዛት ቢሆን፥ እንቅልፍንና ሕልምንም በመውደድ ቢሆን፥ 5 መጠጥንና ስካርን በማብዛት ቢሆን፥ ስድብንና ቍጣንም በማብዛት ቢሆን፥ ቡዋልትንና ቀልድን በመናገርም ቢሆን፥ 6 ባልንጀራቸውንም በማማት በጠብ ቢሆን፥ መልከ መልካሞች የሆኑ የዚህን ዓለም ሴቶችን በማየትም ቢሆን፥ የሚያስትዋቸውን የሽቱዎችን መዓዛ በማሽተትም ቢሆን፥ 7 መዳንን እንዳይችሉ በዚህ ሁሉ እኔ እጣላቸዋለሁ፤ በእነርሱም ምክንያት ከመንበሬ ወደ ተዋረድሁበት ጥፋት ከእኔ ጋራ ይገቡ ዘንድ ከእግዚአብሔር መንገድ አርቃቸዋለሁ። 8 ነቢዩም እንዲህ አለ፥ “አንተ ጥፉና አጥፊ! በትዕቢትህና በልብህ ደንዳናነት፥ ፈጣሪህን በማሳዘንና ፈጣሪህንም ባላማመስገን አንተ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ወጥተህ በካድህ ጊዜ በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ እንዲህ ትታበያለህን? 9 ፈጣሪህ በተቈጣህ ጊዜ ስለ ክፉ ሥራህ ጣለህ፤ ፈጣሪው ከመሬትና ከትቢያ የፈጠረውን፥ እንደ ወደደም የሠራውንና ለምስጋናው ያኖረውን ምስኪን ለምን ትወስደዋለህ? 10 “ረቂቅ የምትሆን አንተ ከእሳት ነበልባልና ከነፋስ የፈጠረህን ፈጣሪ ነኝ በማለት በታበይህ ጊዜ፥ 11 አንተም በተመካህ ጊዜ እግዚአብሔር ክፉ ሥራህን ተመለከተ፤ ሳያጓድል ስሙን ያመሰግን ዘንድ፥ በአንተ ፋንታ የሚያመሰግን አዳምን ፈጠረው፤ አንተ ከሠራዊቶችህ ጋራ እግዚአብሔርን ክደሃልና። 12 አዳምና ልጆቹም እግዚአብሔር ስለ ትዕቢትህ በናቃችሁ በአንተና በሠራዊትህ ምስጋና ፋንታ የእግዚአብሔርን ስም ያመሰግኑ ዘንድ ተፈጠሩ፤ ከሊቃነ መላእክት ሁሉ ይልቅ ራስህን አኵርተሃልና። 13 ስለዚህም እግዚአብሔር እንደ አንተ ከአሉ ከመላእክት አለቆች ሁሉ ለይቶ አዋረደህ፤ በአንድ ምክር የተፈጠራችሁ አንተና ሠራዊትህም ስለማይጠቅም ስለ ልቡናችሁ መደንደንና ስለ ሕሊናችሁ ትዕቢት ከእግዚአብሔር ምስጋና ወጥታችሁ ሳታችሁ፤ በሌላም ሳይሆን በፈጣሪያችሁ ላይ ታበያችሁ። 14 ስለዚህም በትሑታን ይመሰገን ዘንድ አዳምን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ ከበለስም ፍሬ እንዳይበላ ትእዛዝንና ሕግን ሰጠው። 15 በፈጠረውም ሁሉ ላይ ሾመው፤ እንዲህም ብሎ አስታወቀው፤ “በገነት ውስጥ ከአለው ዛፍ ሁሉ ብላ፤ በራስህም ላይ ሞትን እንዳታመጣ የሞት እሾህ ከሆነችው ከአንዲት ዛፍ አትብላ፤” 16 ይህቺንም ቃል በሰማሃት ጊዜ ከአዳም የጎን አጥንት በተገኘች በሔዋን ላይ የአፍህን መርዝ ተፋህ። 17 እንደ አንተም ሕግ አፍራሽ ታደርገው ዘንድ በክፉ ሽንገላ ንጹሑን በግ ነጠቅኸው። 18 እንደ የዋህ ርግብ ሆና የተፈጠረች ተንኰልህን የማታውቅ ሔዋንንም ባሳትሃት ጊዜ በተከናወነ ነገርህና በጠማማ ቃልህ አስካድሃት፤ ያችንም መጀመሪያዪቱን ፍጥረት ካሳትሃት በኋላ፥ እርሷ ሄዳ ከመሬት የተፈጠረ መጀመሪያውን የእግዚአብሔር ፍጥረት አዳምን አሳተችው። 19 በትዕቢትህም ወደማይገባ ሁከት ጨመርኸው፤ የፈጣሪውንም ቃል እንዲክድ አደረግኸው፤ በትዕቢትህም ድሃውን አጠፋኸው። 20 በተንኰልህም ከፈጣሪው ፍቅር አራቅኸው፤ በምክንያትህም ከደስታ ገነት አወጣኸው፤ በመሰናክልህም የገነትን መብል አስተውኸው። 21 በሐሰትህም ከገነት መጠጥ አስጠማኸው፤ አንተ ፍዳ ወደምትቀበልባት ወደ ሲኦል ታወርደው ዘንድ ካለመኖር ወደ እውነተኛ መኖር ካመጣው አምላኩም ፍቅር ታወጣው ዘንድ የዋህ አዳምን ከጥንት ጀምሮ አንተ ተጣልተኸዋልና። 22 መሬታዊም ሲሆን በነፍሱና በሥጋው፥ በልቡናውም ፈጣሪውን የሚያከብርና የሚያመሰግን መንፈሳዊና ተናጋሪ አደረገው። 23 እንደ በገና በተለያዩ ብዙ ስልቶች የሚያመሰግኑ ዐሥር ሕሊናትን ፈጠረለት። |