ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ግፈኛና አሳች፥ የፈጣሪውንም መንገድ የሚፃረር ዲያብሎስን ስለሚበቀለው በኋላ ዘመን ስለሚመጣው ቸርና የዋህ የግብጽ ደሴቶች ደስ ይላቸዋል። 2 እርሱም ይበቀለዋል፤ በልቡናውም ታብዮአልና ክብሩን ወደ መሬትና ወደ መዋረድ ይመልሳል። 3 እርሱም እንዲህ አለ፥ “ከእኔ በላይ ማን ነው? ወደ ባሕሩ ጥልቅ እገባለሁና፥ ወደ ሰማይም እወጣለሁና፥ ጥልቆችንም አያለሁና፥ የአዳምንም ልጆች እንደ ወፍ ጫጩት ጨብጬ እይዛቸዋለሁና። 4 ከቀናች ሕገ እግዚአብሔር አርቃቸው ዘንድ በእነርሱ ላይ ምክንያት ስለምፈጥር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ባላደረጉ፥ በምድር ላይ በሚኖሩ ሰዎች እኔ እበረታታባቸዋለሁና ከእጄ የሚያስጥለኝ የለም። 5 ከእኔ ጋራም ወደ ጥፋት እንዲሄዱ ጐጣጕጥ ወደ ሆነ ጎዳና እመልሳቸዋለሁ። 6 “ስለዚህም እርሱን የወደዱት፥ ሕጉንም የጠበቁ ሰዎች እኔን ይጠላሉ፤ ከጌታቸው ተለይተው የሳቱ ሰዎች ግን ወደ እኔ ይመጣሉ፤ እኔንም ይወድዳሉ፤ ቃል ኪዳኔንም ይጠብቃሉ፤ ወደ ፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔርም እንዳይመለሱ ልባቸውን አከፋለሁና፥ አሳባቸውንም አጠማለሁና እኔ እንዳዘዝኋቸው ትእዛዜን ያደርጋሉ። 7 የዚህን ዓለም ገንዘብ ባሳየኋቸውም ጊዜ ከቀናች መንገድ ልቡናቸውን አስታለሁ፤ መልከ መልካም ሴቶችንና ቆነጃጅትንም ባሳየኋቸው ጊዜ በእነዚህ ከቀናች መንገድ አርቃቸዋለሁ። 8 የሚያንፀባርቁ የሕንደኬ ዕንቆችን፥ ወርቅንና ብርን ባሳየኋቸው ጊዜ ወደ እኔ ሥራ ይመለሱ ዘንድ በዚህም ከቀናችው መንገድ አርቃቸዋለሁ። 9 ቀጭን ልብስን፥ ነጭ ሐርንና ቀይ ሐርን፥ ግምጃንና የተልባ እግርን ባሳየኋቸው ጊዜ በዚህም ከቀናች መንገድ አርቃቸዋለሁ፤ ወደ እኔም አሳብ እመልሳቸዋለሁ፤ ገንዘብን፥ ከብቶችንም እንደ አሸዋ አብዝች ባሳየሁአቸው ጊዜ በዚህም ወደኔ ሥራ እመልሳቸዋለሁ። 10 ስለ ሴቶች፥ ስለ ቍጣና ስለ ጠብ፥ የትዕቢት ቅናትን ባሳየኋቸው ጊዜ በዚህ ሁሉ ወደ እኔ መንገድ እመልሳቸዋለሁ። 11 ምልክቶችንም ባሳየኋቸው ጊዜ በባልንጀሮቻቸው ልቡና አድራለሁ፤ በልቡናቸውም እየራሱ የሆነ የምልክት ነገርን አሳድራለሁ፤ የቃላቸውንም ምልክት አሳይች አስታቸዋለሁ። 12 ማደሪያዬም ላደረግኋቸው ሰዎች ምልክትን አሳያቸዋለሁ፤ በከዋክብት አካሄድም ቢሆን፥ ወይም በደመና መውጣት፥ ወይም በእሳት ማናፋት፥ ወይም በአውሬዎችና በወፎች ጩኸት እነርሱ ማደሪያዎች ናቸውና በዚህ ሁሉ በልቡናቸው ምልክቶችን አሳድርባቸዋለሁ። 13 እነርሱ ተናግረው ለባልንጀሮቻቸው ምልክት ይሰጧቸዋል፤ እኔም ቀድሜ እነዚያ ሟርተኞቻቸው እንደ ነገሯቸው ምልክት እሆናቸዋለሁ። 14 “የመረመሯቸው ሰዎች ይስቱ ዘንድ፥ ዋጋንም ይሰጧቸው ዘንድ፥ እንደ ተናገሩት የሚደረግላቸው ትንቢትንም የሚያውቁ፥ ክፉና በጎንም የሚለዩ፥ ሁሉም እንደ ተናገሩ የሚሆንላቸው፥ እንደ ቃላቸውም የሚደረግላቸው እንደ እገሊትና እንደ እገሌ ዐዋቆች የሉም ብለው ለባልንጀሮቻቸው ይነግሯቸው ዘንድ የቃላቸውን ምልክት አደርግላቸዋለሁ። 15 የሚጠፉ፥ በእኔም የሚስቱ ሰዎች ፈጽመው ይበዙ ዘንድ፥ የአዳምም ልጆች ከእኔ ጋር ይጠፉ ዘንድ ይህን በተናገሩ ጊዜ እኔ ደስ ይለኛል፤ ለበታች አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለ አባታቸው ስለ አዳም ከክብሬ አዋርዶኛልና። 16 “እኔም በትእዛዜ የሚሄዱ ልጆቹን ሁሉ ወደ ጥፋት እወስዳቸዋለሁ” ያሳትኋቸው ሰዎች ከእኔ ጋራ በእሳት ውስጥ ይጨመሩ ዘንድ ከፈጠረኝ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን አለኝ። 17 እኔም ቍጣውን በእኔ ላይ ባበዛ ጊዜ፥ አስረውም ወደ ገሃነምና ወደ ሲኦል ጥልቅ ይጥሉኝ ዘንድ ባዘዘ ጊዜ፥ ጌታዬን ማለድሁ፤ ፈጣሪዬም እንዲህ በአዘዘ ጊዜ ተቈጥተኸኛልና በመቅሠፍትህም ገሥጸኸኛልና፥ በመዓትህም ቀሥፈኸኛልና አቤቱ ጌታዬ በፊትህ አንዲት ነገር እናገር ዘንድ ፍቀድልኝ ብዬ በፊቱ ማለድሁ። 18 ጌታዬም፦ ተናገር እሰማሃለሁ ብሎ መለሰለኝ፥ ያንጊዜም ወደ እርሱ እንዲህ እያልሁ እለምን ጀመርሁ። ከክብሬ ከተዋረድሁ በኋላ ያሳትኋቸው ሰዎች እኔ መከራ በምቀበልበት ከእኔ ጋር ይሁኑ። 19 ነገር ግን እንቢ ያሉኝ፥ በእኔም ያልሳቱ፥ ትእዛዝህን ያደርጉ ዘንድ፥ ፈቃድህንም ይፈጽሙ ዘንድ፥ ቃልህንም ይጠብቁ ዘንድ፥ ትእዛዜን ያልጠበቁ፥ እኔም እንዳስተማርኋቸው እንቢ ባሉ ጊዜ፥ እኔም እንዳሳትኋቸው በእኔ ባልሳቱ ጊዜ እነርሱ ለመንግሥትህ ይሁኑ፤ ትወድደኝም በነበረ ጊዜ ለእኔ የሰጠኸኝን ዘውድ ይውሰዱ። 20 ከእኔ ጋር ላልተሰደዱና ሰይጣናት ላልተባሉ ሥልጣናትም የእኔን ዘውድ ስጣቸው፤ ከእኔና ከሠራዊቶችም ባዶ በሆነች መንበሬ በቀኝህ አስቀምጣቸው። 21 እንደ ወደድህም ያመስግኑህ፤ እንደ እኔና እንደ ሠራዊቶች ይሁኑ፤ እኔን ጠልተህ ከአመድና ከመሬት የተፈጠሩትን ስለ ወደድሃቸው፥ የእኔ ሥልጣን ተሽሮአልና፥ የእነርሱም ሥልጣን ከፍ ከፍ ብሏልና እንደ ወደድህ ያመስግኑህ።” 22 ጌታዬም መልሶ እንዲህ አለኝ፥ “እያዩና እየሰሙ ሥራዬን ሳይወዱ አንተ አስተሃቸዋልና እንደ ፈቃድህና እንደ ቃልህ ይሁኑህ። 23 ትእዛዜንና የመጻፎችን ቃል ትተው ወደ አንተ ከመጡ ጥፋታቸው አያሳዝነኝም፤ አንተም ከአሳትሃቸው ከአንተ ጋር በገሃነም ይቀጡ። 24 እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ለአንተና በአንተ ለሳቱ ከገሃነም ቅጣት መውጫ የላችሁም። ነገር ግን ለዘለዓለም በእሳት ውስጥ ትሠቃያላችሁ። |