2 ሳሙኤል 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ለብዙ ጊዜ ጦርነት ሆነ፤ የዳዊት ቤት እየበረታ፥ የሳኦል ቤት ግን እየደከመ የሚሄድ ሆነ። 2 ለዳዊትም ወንዶች ልጆች በኬብሮን ተወለዱለት፤ በኵሩም ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን ነበረ። 3 ሁለተኛውም ከቀርሜሎሳዊቱ ከአቤግያ የተወለደው ዶሎሕያ ነበረ። ሦስተኛውም ከጌድሶር ንጉሥ ከቶልሜልም ልጅ ከመዓክ የተወለደው አቤሴሎም ነበረ። 4 አራተኛውም የአጊት ልጅ አዶንያስ፥ አምስተኛውም የአቢጣል ልጅ ሰፋጥያ ነበረ። 5 ስድስተኛውም የዳዊት ሚስት የዒገል ልጅ ይትረኃም ነበረ። ለዳዊት በኬብሮን የተወለዱለት እነዚህ ነበሩ። አበኔር ወደ ዳዊት እንደ ገባ 6 በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ጦርነት ሆኖ ሳለ አበኔር የሳኦልን ቤት ያበረታ ነበር። 7 ለሳኦልም የኢዮሄል ልጅ ሩጻፋ የተባለች ዕቅብት ነበረችው፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፥ “ወደ አባቴ ዕቅብት ለምን ገባህ?” አለው። 8 አበኔርም ኢያቡስቴ እንዲህ ስላለው እጅግ ተቈጣ፤ አበኔርም እንዲህ አለው፥ “በውኑ እኔ የውሻ ራስ ነኝን? እኔ ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹም፥ ለዘመዶቹም ቸርነት አድርጌአለሁ፤ አንተንም ለዳዊት እጅ አሳልፌ አልሰጠሁህም፤ አንተም ዛሬ ከዚህች ሴት ጋር ስለ ሠራሁት ኀጢአት ትከስሰኛለህ። 9 እግዚአብሔር ለዳዊት እንደ ማለለት እንዲሁ ከእርሱ ጋር ዛሬ ባላደርግ እግዚአብሔር በአበኔር ይህን ያድርግበት፤ ይህንም ይጨምርበት። 10 የዳዊትንም ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ከፍ ያደርግ ዘንድ መንግሥትን ከሳኦል ቤት ወሰዳት።” 11 ኢያቡስቴም አበኔርን ይፈራው ነበርና ቃልን ይመልስለት ዘንድ አልቻለም። 12 አበኔርም ለዳዊት፥ “ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፤ እጄም ከአንተ ጋር ትሆናለች፤ እስራኤልንም ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ” ብለው በስሙ ይነግሩት ዘንድ መልእክተኞችን ወዲያውኑ ላከለት። 13 ዳዊትም፥ “ይሁን፤ በመልካም ፈቃደኛነት ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር ከአንተ እሻለሁ፤ ፊቴን ለማየት በመጣህ ጊዜ፥ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ካላመጣህልኝ ፊቴን አታይም” አለው። 14 ዳዊትም ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ፥ “በመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ያጨኋትን ሚስቴን ሜልኮልን መልስልኝ” ብሎ መልእክተኞችን ላከ። 15 ኢያቡስቴም ልኮ ከሴሊስ ልጅ ከባልዋ ከፈላጥያል ወሰዳት። 16 ባልዋም እያለቀሰ ከእርስዋ ጋር ሄደ፤ እስከ ብራቂም ድረስ ተከተላት። አበኔርም፥ “ሂድ፤ ተመለስ” አለው፤ እርሱም ተመለሰ። 17 አበኔርም ለእስራኤል ሽማግሌዎች፥ “አስቀድሞ ዳዊት በእናንተ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ፈልጋችሁ ነበር። 18 እግዚአብሔርም ስለ ዳዊት፦ በባሪያዬ በዳዊት እጅ ሕዝቤን እስራኤልን ክፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ አድናለሁ ብሎ ተናግሮአልና እንግዲህ አሁን አድርጉ´ ብሎ ነገራቸው። 19 አበኔርም ደግሞ በብንያም ልጆች ጆሮ ተናገረ፤ አበኔርም ደግሞ በእስራኤልና በብንያም ቤት ሁሉ መልካም የነበረውን ለዳዊት ሊነግረው ወደ ኬብሮን ሄደ። 20 አበኔርም ከሃያ ሰዎች ጋር ወደ ዳዊት ወደ ኬብሮን መጣ፤ ዳዊትም ለአበኔርና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። 21 አበኔርም ዳዊትን፥ “ተነሥቼ ልሂድ፤ ካንተ ጋርም ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፥ ነፍስህም እንደ ወደደች ሁሉን እንድትገዛ እስራኤልን ሁሉ ለጌታዬ ለንጉሥ ልሰብስብ” አለው። ዳዊትም አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ። አበኔር እንደ ተገደለ 22 በዚያ ጊዜም የዳዊት ብላቴኖችና ኢዮአብ ከዘመቻ ታላቅ ምርኮ ይዘው መጡ። አበኔር ግን ዳዊት አሰናብቶት በደኅና ሄዶ ነበር እንጂ በኬብሮን አልነበረም። 23 ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረ ጭፍራ ሁሉ በመጡ ጊዜ፥ “የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሥ መጣ፤ አሰናበተውም፤ በሰላምም ሄደ” ብለው ሰዎች ለኢዮአብ ነገሩት። 24 ኢዮአብም ወደ ንጉሥ ገብቶ፥ “ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? እነሆ፥ አበኔር መጥቶልህ ነበር፤ በደኅና እንዲሄድ ስለምን አሰናበትኸው? 25 የኔር ልጅ አበኔር ያታልልህ ዘንድ፥ መውጫህንና መግቢያህንም ያውቅ ዘንድ ፥ የምታደርገውንም ነገር ሁሉ ያስተውል ዘንድ እንደ መጣ አታውቅምን?” አለው። 26 ኢዮአብም ከዳዊት በወጣ ጊዜ መልእክተኞችን ከአበኔር በኋላ ላከ፤ ከሴይርም ጕድጓድ መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም። 27 አበኔርም ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ ኢዮአብ በበር ውስጥ በቈይታ ይናገረው ዘንድ ወደ አጠገቡ ወሰደው፤ በዚያም ለወንድሙ ለአሣሄል ደም ተበቅሎ ወገቡን መታው፤ ሞተም። 28 ከዚህም በኋላ ዳዊት ሰማ፤ እንዲህም አለ፥ “ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በእግዚአብሔር ዘንድ ለዘለዓለም እኔ ንጹሕ ነኝ፤ መንግሥቴም ንጹሕ ነው፤ 29 በኢዮአብ ራስ ላይና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይምጣበት፤ በኢዮአብም ቤት ፈሳሽ ነገር ያለበት ወይም ለምጻም ወይም አንካሳ ወይም በሰይፍ የሚወድቅ ወይም እንጀራ የሌለው ሰው አይታጣ።” 30 ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳም በሰልፍ በገባዖን ወንድማቸውን አሣሄልን ገድሎ ነበርና አበኔርን ይገድሉት ዘንድ ይጠባበቁ ነበር። 31 ዳዊትም ኢዮአብንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሁሉ፥ “ልብሳችሁን ቅደዱ፤ ማቅም ልበሱ፤ በአበኔርም ፊት አልቅሱ” አላቸው። ንጉሡም ዳዊት ከቃሬዛው በኋላ ሄደ። 32 አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ በመቃብሩ አጠገብ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ ለአበኔር አለቀሱለት። 33 ንጉሡም ለአበኔር አለቀሰለት፤ እንዲህም አለ፦ “አበኔር ሰነፍ እንደሚሞት ይሞታልን? 34 እጆችህ አልታሰሩም፤ እግሮችህም በሰንሰለት አልተያዙም፤ ማንም እንደ ሰነፍ አልወሰደህም፤ በዐመፃ ልጆችም ፊት ወደቅህ።” ሕዝቡም ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት። 35 ሕዝቡም ሁሉ ገና ሳይመሽ ዳዊትን እንጀራ ይበላ ዘንድ ሊጋብዙት መጡ፤ ዳዊት ግን፥ “ፀሐይ ሳትጠልቅ እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ” ብሎ ማለ። 36 ሕዝቡም ሁሉ ይህን ዐወቁ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት ንጉሥ ያደረገው ሁሉ ደስ አሰኛቸው። 37 በዚያም ቀን ሕዝቡ ሁሉ እስራኤልም ሁሉ የኔር ልጅ አበኔርን እንዲገድሉት ንጉሡ እንዳላዘዘ ዐወቁ። 38 ንጉሡም ብላቴኖቹን፥ “ዛሬ በእስራኤል ዘንድ ታላቅ መኰንን እንደ ወደቀ አታውቁምን? 39 እኔም ዛሬ ዘመዱ እንደ ሆንሁ፥ እርሱም በንጉሡ ዘንድ የተሾመ እንደ ሆነ አታውቁምን? እነዚህም ሰዎች የሦርህያ ልጆች በርትተውብኛል፤ እግዚአብሔርም ክፋት በሠራ ላይ እንደ ክፋቱ ይመልስበት” አላቸው። |