ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እግዚአብሔር ያይደለህ አንተ ደካማ ሰው ሆይ! ለምን ትኰራለህ? ዛሬ ሰው ነህ፤ ነገም መሬትና ዐመድ ነህ፤ በመቃብርህም ትልና ብስባሽ ትሆናለህ። 2 ዳግመኛም አንተንና የአንተን ሥራ የሚሠሩትን ሲኦል ትከተላቸዋለች፤ የአንተ መምህር አባታችን አዳምን ስለ አሳተ የዐለምን ሁሉ ኀጢአት ወደ ራሱ የሚመልስ ሰብልያኖስ ነውና፤ 3 ራሱንም በማኵራትና ልቡናውን በማደንደን ለፈጣሪው ሥራ መስገድን እንቢ ብሏልና። 4 አንተም እንደ መምህርህ ለፈጣሪህ ለእግዚአብሔር መስገድን እንቢ ብለሃል። 5 አንተም ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን የማያውቁት የቀደሙህ እንደ ሄዱት ትሄዳለህ፤ 6 በምድር ስለ ሠሩት ስለ ክፉ ሥራቸው እንደ ተበቀላቸውና ወደ ሲኦል እንደ ወረዱ፥ 7 አንተም እንደ እነርሱ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ። 8 ቍጣውንም አነሣሥተሃልና፥ በአምስቱም መንግሥታት ላይ ሥልጣንን የሰጠህ እግዚአብሔርን ማምለክ ቸል ብለሃልና፥ ከእግዚአብሔር እጅ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 9 ፈቃዱንም ታደርግ እንደ ሆነ፥ አታደርግም እንደ ሆነ መረመረህ፤ በምድርም መንገድህን ብታሣምር እግዚአብሔር መንገድህን ያከናውንልሃል፤ እጅህንም ያኖርህበትን ሁሉ ያከናውንልሃል፤ ይባርክልሃልም፤ ጥንተ ጠላቶችህንና የዕለት ጠላቶችህንም ያስገዛልሃል። 10 በመውጣትህና በመግባትህ፥ በሆድህም ፍሬ፥ በመንጋዎችህና በድልቦችህም፥ በጣቶችህም በአመለከትህበት ሥራ ሁሉ፥ በልብህም ባሰብኸው ሁሉ ደስ ይልሃል፤ እንዲህ ታደርግ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል፥ ታፈርስም ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሥልጣን ተሰጥቶሃልና ሁሉ ይታዘዝልሃል። 11 ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃልና ሕግ መስማትን እንቢ ብትል፥ በፍርዱም ባትኖር ፍርዱ ሁሉ እውነት ነውና ከአንተ አስቀድሞ እንደ ነበሩ፥ በሚገባም እግዚአብሔርን እንደማያመልኩት፥ በቀና ፍርዱም ጸንተው እንዳላመኑ ወንጀለኞች ከእግዚአብሔር እጅ የምታመልጥበት የለም። 12 ከፊቱም የሚሰወር የለም፤ ነገር ግን ሁሉ በፊቱ ፈጽሞ የተገለጠ ነው። 13 የነገሥታቱን ሥልጣን የሚይዝና የኀይለኞችን ዙፋን የሚገለብጥ እርሱ ነው። 14 የተዋረዱትንም ከፍ ከፍ የሚያደርግ፥ የወደቁትንም የሚያነሣ እርሱ ነው። 15 የታሰሩትን የሚፈታ እርሱ ነው፤ የሞቱትንም የሚያስነሣ እርሱ ነው፤ የይቅርታ ጠል ከእርሱ ዘንድ ነውና ሥጋቸው የፈረሰና የበሰበሰ፥ እንደ ትቢያም የሆነ ሰዎችን በወደደ ጊዜ ያስነሣቸዋል። 16 አሳዝነውታልና ክፉ ሥራ የሠሩ ሰዎችንም የደይን ትንሣኤን ያስነሣቸዋል፤ ይበቀላቸዋልም። 17 በምድርም ዘራቸውን ያጠፋል፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን ሕጉንና ሥርዐቱን ያፈረሱ ናቸውና፤ 18 የጻድቃን መንገድ ከኃጥኣን መንገድ ይልቅ ጭንቅ ነውና ኃጥኣን በጻድቃን ምክር ይኖሩ ዘንድ አይወድዱም። 19 ሰማይ ከምድር የራቀ እንደ ሆነ እንደዚሁ የጻድቃን መንገድ ከኀጥኣን መንገድ የራቀ ነው። 20 የኃጥኣን መንገድ ግን የቅሚያና የክፋት፥ የዐመፅና የዝሙት፥ የስስትና የክዳት ነው፤ በዐመፅም መስከርና የሰውን ገንዘብ መቀማት ነው። 21 የሰውን ደም ወደ ማፍሰስ ፈጥኖ መሔድ፥ በማይጠቅም ጥፋት ማድረግ፥ ድሃአደጉን ማስለቀስ፥ ደምንና ሞቶ ያደረውን መብላት፥ የግመልና የእሪያም ሥጋ መብላት፥ ወደ አራስና ሳትነጻ በደሟ ወዳለች ሴት መሔድ ነው። 22 ይህም ሁሉ የኃጥኣን ሥራ ወደ ዘለዓለም ጥፋትና ቅጣት የሚወስድ ሰፊ መንገድና የተዘረጋ የሰይጣን ወጥመድ ነው። 23 ጠባብና ቀጭን የምትሆን የጻድቃን ጎዳና ግን ወደ ሕይወት፥ ወደ የዋህነትና ወደ ትሕትናም፥ ወደ ፍቅርና ሰላም፥ ወደ ጾምና ጸሎት፥ ወደ ሥጋም ንጽሕና፥ ከማይጠቅም፥ አባላ የተመታውንና ሞቶ ያደረውን ከመብላት፥ ወደ ጐልማሳ ሚስት ከመሔድና ከዝሙትም ወደ መጠበቅ የምትወስድ ናት። 24 ኀጢአተኞች ሰዎች ይኸን ሁሉ ያደርጋሉና በሕግ ከአልታዘዘ ከተጠላ ሥራ ሁሉና ርኩስ መብልን ከመብላት፥ እግዚአብሔርም ከማይወደው ሥራ ሁሉ ይጠበቃሉ። 25 ጻድቃን እግዚአብሔር ከማይወደው መንገድ ሁሉ ይርቃሉ። 26 እርሱም ይወድዳቸዋል፤ ከመከራቸውም ሁሉ እንደ አደራ ገንዘብ ይጠብቃቸዋል፤ ያድናቸዋልም። 27 ኃጥኣንን ግን ሰይጣን ይገዛቸዋል። ሕጉንና ሥርዐቱን፥ የሚወደውንም ሁሉ ይጠብቃሉና። |