ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በትዕቢትና በልብ ተንኰል ሄደ። 2 በመንግሥቱም ዳንኤል እንዳየው ብረት ፅኑ ተብሏልና በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሀገሮችን ዞረ። 3 በስንፍናና በክፋት ሁሉ፥ በሁከትም ይኖራል። 4 ቀድሞም የተናገርነውን ይሰብራል፥ ያደቅቃል፤ ይበላልም። 5 አንገቱን እንደ አደነደነ እንደ አባቱ እንደ ዲያብሎስም መርዝ የሚተፋ ነውና የቀረውን በእግሩ ይረግጣል። 6 እግዚአብሔርንም ፈጣሪው እንደ ሆነ አያውቀውም፤ ነገር ግን ዘመኔ እንደ ሰማይ ዘመን ሆነ ይላል። 7 በልቡናውም ፀሐይ ከእርሱ እንደሚወጣ ያስባል። 8 በኀይልም ይነሣል፤ በዛብሎን ዕጣ ይሰፍራል፤ በመቄዶንያም ሰልፍን ያስነሣል፤ ከሰማርያም ቀለቡን ይቀበላል፤ ከሶርያም እጅ መንሻን ይሰጡታል። 9 በዘላኖች አውራጃ ይሰፍራል፤ እስከ ሲዶናም ይደርሳል፤ በአካይያም ግብርን ይጥላል፤ እስከ ፈሳሹ ባሕርም ድረስ አንገቱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ተመልሶም እስከ ሕንደኬ ባሕር ድረስ መልእክቱን ይልካል። 10 እንዲሁም አንገቱን እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ከፍ ያደርጋል። 11 በመታበይና በክፋት ጸንቶ ይኖራል እንጂ ራሱን ማዋረድ የለውም። 12 መንገዱም ሁሉ ወደ ጨለማና ወደ ድጥ፥ ወደ ወንጀልና ወደ መታበይም፥ ደም ወደ ማፍሰስና ወደ መከራም ነው። 13 መንገዱ ሁሉ እግዚአብሔር የሚጠላው ነው፤ የቅሚያና የክፋት፥ የኀጢአትም መምህር ሰብላንዮስ እንደ አስተማረው ያደርጋል፤ ድሃአደጉንም ያስጮሃል፤ ለድሃም አይራራም። 14 የአሕዛብንም ነገሥታት በእጁ አግብቶ ገደላቸው። 15 የጠላቶች አለቆችንም ገዛ፤ ብዙ አሕዛብንም ገዛ፤ እንደ ወደደም አስገበራቸው። 16 ምሕረትም አላደረገም፤ ከተርሴስ ባሕር ጀምሮ እስከ ኢያሪኮ ባሕር ድረስ ያልነጠቀው የለም። 17 ለጣዖትም ይሰግድ ነበር፤ ሙቶ ያደረውንና ደሙን፥ አባላ የተመታውንና ለጣዖቶች የተሠዋውን ይበላ ነበር፤ በሥራውም ሁሉ ያለ ፍርድ ፍጹም ቍጣና ክርክር ነበር እንጂ ፍርድ አልነበረውም። ከሥልጣኑ በታች ላሉ አሕዛብም የሚያስደነግጥ ሆኗልና እንደ ወደደ ግብርን ያስገብራቸው ነበር። 18 በፊቱ የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና በፊቱ እግዚአብሔርን መፍራት አልነበረውም፤ በፈጣሪው በእግዚአብሔርም ፊት በተንኰል ይኖር ነበር። 19 እንደ ፈጣሪውም አያደርገውም ነበር። እግዚአብሔርም ተቈጥቶ በያዘው ጊዜ በባልንጀራው ላይ ክፉ ነገርን እንደ አደረገ ፍዳውን ይከፍለዋል። 20 እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም ስም አጠራራቸውን አጠፋ ዘንድ በትእዛዜ የማይኖሩ ትዕቢተኞችን እኔ ተበቅዬ አጠፋቸዋለሁ ብሏልና፥ ከእርሱ አስቀድሞ የነበሩ ኃጥኣንን እንዳጠፋቸው በጊዜው ይበቀለዋል። 21 ክፉዎችም ክፉ እንደ አደረጉ ፍዳቸውን ይቀበላሉ። 22 በጎ አድራጊዎችን ግን በጎነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ትከተላቸዋለች። 23 ኢያሱ አምስቱን የከነዓን ነገሥታትን በአንዲት ቀን በአንዲት ዋሻ እንደ አጠፋቸው፥ ሠራዊቶቻቸውንም ያጠፋቸው ዘንድ በጸሎቱ ፀሐይን በገባዖን እንደ አቆመ፥ የኤዌዎንንና የከናኔዎንን፥ የፌርዜዎንንና የኬጤዎንን፥ የኢያቡሴዎንንም ሠራዊት እስኪያጠፋቸው ድረስ ፀሐይ በሰማይ መካከል ቆሟልና በአንድ ጊዜ ሃያ ሺህ ያህል ሰውም እንደ ገደለ፥ እነርሱንም እንደ ገደላቸው፥ እግር ከአንገትም አድርጎ እንደ አሰራቸው፥ በዋሻም በጦር እንደ ገደላቸው፥ ደንጊያም እንደ ገጠመባቸው፥ 24 በክፉ ሥራቸው እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑትንም ሰዎች እንደዚህ ያለ መከራ ያገኛቸዋል። |