ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የሞዓብ ሬማት ለሶርያ ቅርብ ናትና ነቢዩ ነገረው። 2 ጕድጓድም ቈፍሮ እስከ አንገቱ ገባ፤ መራራ ልቅሶንም አለቀሰ፤ በእግዚአብሔር ፊት ስለ ሠራው ኀጢአቱም ንስሓ ገባ። 3 እግዚአብሔርም ነቢዩን እንዲህ አለው፤ “ከይሁዳ ሀገር ወደ ሬማት ወደ ሞዓቡ ሹም ወደ መቃቢስ ተመለስ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል በለው፦ በኀይሌ ጽናትና በሠራዊቴ ቅድስቲቱን ከተማ አጠፋኋት እንዳትል ከተማዬን ታጠፋ ዘንድ የአንተ ፈጣሪ እኔ እግዚአብሔር በፈቃዴ ላክሁህ እንጂ ይህን ነገር ያደረግኸው አንተ አይደለህም፤ 4 በስስትዋ ሁሉ፥ በክዳትዋና በሴሰኝነትዋም አሳዝናኛለችና። 5 እኔም ቸል ብዬ በአንተ እጅ አሳልፌ ሰጠኋት፤ አንገትህን ስለ አደነደንህ፥ ከተማዪቱንም በእጄ ብርታት ከበብኋት ስለምትል ስለ አንተ አይደለም። አሁንም ስለ ወለድሃቸው ልጆችህ እግዚአብሔር ኀጢአትህን ይቅር አለህ። 6 አሁንም በፍጹም ልቡናህ ጨክነህ ንስሓ ግባ። የሚጠራጠሩ ሰዎች ንስሓ ለመግባት አይጨክኑምና ተጠራጣሪ አትሁን። 7 ነገር ግን በፍጹም ልቡናቸው ንስሓ የሚገቡ፥ ስለ ክፋታቸውም ንስሓ በገቡበት ሁሉ ወደ ጥመትና ወደ ኀጢአት የማይመለሱ ሰዎች ብፁዓን ናቸው። 8 በልቅሶና በኀዘን፥ በብዙ ልመናና በስግደትም ወደ ፈጠራቸው ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ የሚጨክኑም ብፁዓን ናቸው፤ ንስሓ የገቡትን ከሳታችሁ በኋላ ንስሓ የገባችሁ እናንተ የእኔ ናችሁ ብሏቸዋልና፤ 9 ትዕቢተኛውንም ከሳተ በኋላ በንስሓ ወደ እርሱ በተመለሰ ጊዜ ስለ ፍርሀትህና ስለ ድንጋጤህ ኀጢአትህን ይቅር እልሃለሁ አለው፤ የአባትን ኀጢአት በልጆች ላይ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ የማመጣ፥ ለሚወድዱኝ፥ ሕጌንም ለሚጠብቁ ግን ለእነርሱ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝና። 10 አሁንም ስለ ወለድኻቸው ስለ እነዚህ ልጆች ከአንተ ጋራ ያለውን ቃል ኪዳኔን እጠብቃለሁ፤ ስለ ሠራኸው ኀጢአትህም ያደረግኸውን ንስሓ እቀበላለሁ ይላል ሁሉን የሚችል የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር።” 11 ያንጊዜም ከጕድጓዱ ወጣ፤ “እኔ እግዚአብሔርን አሳዝኜዋለሁና የወደድኸውን አድርገኝ እንጂ ከአንተ እንዳልለይ እግዚአብሔር እንዲህና እንዲህ ያድርገኝ ብሎ ለነቢዩ ሰገደ፤ ለእኛ ሕግ የለንምና እንደ አባቶች በትእዛዙ አልሄድሁም፤ አባቶቻችንም እንዳስተማሩን ጣዖት እንደምናመልክ አንተ ታውቃለህ። 12 እኔ በኀጢአቴና በልቡናዬ ትዕቢት የሔድሁ፥ በአንገቴ ደንዳናነትም ፈጣሪዬን ያሳዘንሁ ኀጢአተኛ ነኝና። እስከ አሁንም ድረስ የእግዚአብሔርን ነቢያት ቃል አልሰማሁም ነበር፤ ባዘዘኝም በሕጉና በትእዛዙ አልኖርሁም።” 13 ነቢዩም መልሶ፥ “ከእናንተ አስቀድሞ ከወገናችሁ ኀጢአቱን የታመነ የለምና ዛሬ ንስሓህን እንደ ተቀበለ ዐወቅሁ” አለ። 14 ከእንግዲህ ወዲያ ግን ጣዖት ማምለክን ተው፤ መመለስህ እውነተኛ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ተመለስ፤ ከነቢዩም እግር በታች ሰገደ፤ ነቢዩም አነሣው፤ የሚገባውንም በጎ ሥራ ሁሉ አዘዘው። 15 እግዚአብሔርም እንዳዘዘው አደረገ፤ ወደ ቤቱም ተመለሰ። 16 ያም መቃቢስ አእምሮውን አስተካከለ፤ ከቤቱም ጣዖቱንና ጥንቆላውን፥ ጣዖት የሚያመልኩ ሰዎችንና ሟርተኞችን፥ ጠንቋዮችንም አስወገደ፤ 17 ከኢየሩሳሌም ያመጣቸውንም የምርኮ ልጆች አባቶቻቸው እንደሚያደርጉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ፥ ሥርዐቱንና ሕጉንም ያደርጉ እንደ ሆነ ጧትና ማታ ይመረምራቸው ነበር። 18 ከተማረኩትም ልጆች ከዐዋቂዎቹ በቤቱ ሾመ። 19 ዳግመኛም የእስራኤል ልጆች የሚያደርጉትን የእግዚአብሔርን ሕግ ያስተምሯቸው ዘንድ ወደ መኝታው የሚገቡ፥ ታናናሽ ቅምጥል ልጆቹን የሚጠብቁ ዐዋቂዎችን ከታናናሾቹ ሾመ፤ ሥርዐቱንና ሕጉን፥ አምልኮቱንና ፍርዱን፥ ሞዓባውያንም የሚያደርጉትን ሥርዐት ሁሉ ከምርኮ ልጆች ይሰማ ነበር። 20 መስጊዳቸውን፥ ጥንቆላቸውንና ጣዖቶቻቸውን፥ ጧትና ማታ ከሰቡት ከፍየሎች ጠቦቶችና ከበጎች መንጋዎች፥ ለጣዖታቱ የሚሠዋውን መሥዋዕቱንና ወይኑንም ያጠፋ ነበር። 21 በቀትርና በሰዓት በሥራው ሁሉ ይሰግድላቸውና ያመልካቸው ነበር፤ ይለምናቸውና ይተማመናቸውም ነበር፤ እንዲሁም ከመንገዱ በተመለሰ ጊዜ ይለምናቸው ነበር፤ የጣዖታቱ ካህናትም በነገሩት ሁሉ ፈቃዳቸውን ያደርግ ነበር። 22 በነገሩ ሁሉ የሚያድኑት ይመስለው ነበርና የነገሩትን ሁሉ አይንቅም ነበር። 23 ያ መቃቢስ ግን የእነርሱን መንገድ ተወ። 24 ነቢይ የሚሉት የረኣዩን ነገር ከሰማ በኋላም በንስሓ መንገዱን አሣመረ፤ በዚያም ወራት ወገኖቹ ሁሉ ከእስራኤል ልጆች ይልቅ መንገዳቸውን አሣመሩ፤ የእስራኤል ልጆች አንድ ጊዜ ያሳዝኑት ነበርና በቀሠፋቸውም ጊዜ ዐውቀው ወደ እግዚአብሔር ይጮኹ ነበርና። 25 መከራ በሚያጸኑባቸው በአሕዛብ እጅ ተይዘው እንደ ተዋረዱ፥ ወደ እርሱም እንደ ጮሁ በሰማ ጊዜ የአባቶቻቸውን መሐላ አስቦ የዚያን ጊዜ ስለ አባቶቻቸው ስለ አብርሃምና ስለ ይስሐቅ፥ ስለ ያዕቆብም ይቅር ይላቸው ነበር። 26 በአዳናቸውም ጊዜ ያዳናቸውን ይረሱት ነበር፤ ጣዖታቱንም ወደ ማምለክ ይመለሱ ነበር። 27 ያንጊዜም በመከራ የሚያሠቃዩአቸው አሕዛብን ያስነሣባቸው ነበር፤ በአሠቃዩአቸውና ባሳዘኑአቸውም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጮሁ ነበር፤ የዚያን ጊዜም ራርቶ ይቅር ይላቸው ነበር። የእጁ ፍጥረት ስለ ሆኑ ይወድዳቸው ነበርና። 28 ዳግመኛም በሚጠብቃቸው ጊዜ በዙሪያቸው ያለ ጣዖትን በማምለክና በክፉው የእጃቸው ሥራ ያሳዝኑት ዘንድ ይመለሱ ነበር። 29 እርሱ ግን የኢሎፍሊንና የሞዓብን፥ የምድያምንና የሶርያን፥ የግብፅንም ሕዝብ ያስነሣባቸው ነበር፤ ጠላቶቻቸውም ድል በነሷቸው ጊዜ፥ መከራ በአጸኑባቸውና በአስገበሯቸው ጊዜ፥ በገዟቸውም ጊዜ ይጮሁና ያለቅሱ ነበር፤ እግዚአብሔርም በወደደበት ጊዜ ያድኗቸው ዘንድ መሳፍንትን ያስነሣላቸው ነበር፤ መሳፍንቱም ያድኗቸው ነበር። |