ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የራሳቸው ገንዘብና የእጃቸው ሥራ ያልሆነውን የሌላውን ገንዘብ በዐመፅ የሚሰበስቡ ሰዎች ወዴት አሉ? 2 ያለ ዋጋ የሌላውን ገንዘብ ይወስዳሉና፥ የምትደርስባቸው ዕለተ ሞታቸውንም ሳያውቁ ይሰበስባሉና፥ ገንዘባቸውንም ለባዕድ ይተዋሉና። 3 ልጆቻቸውም በአባቶቻቸው ገንዘብ ደስ አይላቸውም፤ እንደ አባቶቻቸው እንደ እነርሱ ያሉ ኃጥኣንን በስርቆትም ቢሆን በቅሚያም ቢሆን፥ አስጨንቀው የሚይዙ የኃጥኣን ወገኖች ናቸውና። 4 የአባቶቻቸውም ገንዘብ አይጠቅማቸውም፤ በንጥቂያና በግፍ ሰብስበውላቸዋልና፤ እንደ ጉም ሽንትና ነፋስ እንደሚበትነው ጢስም፥ እንደሚረግፍ ሣርም፥ በእሳትም ፊት እንደሚቀልጥ ሰም እንዲሁ የኃጥኣን ክብራቸው ይጠፋል። 5 ዳዊትም እንደ ተናገረ፥ “ኀጢአተኛን እንደ ሊባኖስ ዛፍ ለምልሞና ከፍ ከፍ ብሎ አየሁት፤ በተመለስሁ ጊዜ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁ፤ ቦታውንም አላገኘሁም።” 6 የማይሞቱ መስሏቸው የሌላውን ገንዘብ በግፍ ስለሚሰበስቡ ዛሬ ባልንጀሮቻቸውን የሚበድሉ ሰዎች እንዳይመኩ የኃጥኣን ጥፋታቸው እንደዚህ በአንድ ጊዜ ነው። 7 እናንተ ሰነፎች፥ እንደምታልፉ፥ ገንዘባችሁም ከእናንተ ጋር እንደሚያልፍ አስቡ፤ ወርቃችሁና ብራችሁ ቢበዛ የዛገ ይሆናል። 8 ልጆችን ብታበዙም የመቃብር ብዛት ይሆናል፤ ቤቶችንም ብታበዙ የፈረሰ ይሆናል። 9 የአምላካችሁ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አልፈጸማችሁምና ከብት ብታበዙም ለጠላቶቻችሁ ምርኮ ይሆናል፤ ያልተባረከ ሆኗልና፥ እጃችሁን ያኖራችሁበት ገንዘብ ሁሉ አይገኝም። 10 በቤትም ያለ ቢሆን፥ በዱርም ያለ ቢሆን፥ በመሰማሪያና በእርሻም ያለ ቢሆን፥ በእህል አውድማና በወይን መጭመቂያም ያለ ቢሆን አይገኝም። 11 በሆዳችሁም ፍሬ ቢሆን ደስ አይላችሁም፤ ነገር ግን ከጠላቶቻችሁ የተነሣ ኀዘን ይሆንባችኋል። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላልጠበቃችሁ፥ እግዚአብሔር ከቤተ ሰባችሁ ሁሉ ጋር አያድናችሁምና። 12 ሕጉንና ሥርዐቱን፥ ትእዛዙንም የጠበቁ ሰዎችን ግን ከበረከቱ አያሳጣቸውም፤ የለመኑትንም ሁሉ ይሰጣቸዋል፤ የምድራቸውን ፍሬና የሆዳቸውን ፍሬም ይባርክላቸዋል። 13 እንዲገዙ እንጂ እንዳይገዙ፥ በዙሪያቸው ከአሉ አሕዛብም ሁሉ በላይ ያደርጋቸዋል፤ በመሰምሪያቸውም ቦታ በረከቱን ሁሉ ይሰጣቸዋል። 14 እጃቸውን ያኖሩበትን ሁሉ፥ የእርሻቸውን ፍሬ ሁሉና የከብቶቻቸውን ቦታ ሁሉ ይባርክላቸዋል፤ በሆዳቸውም ፍሬ ደስ ያሰኛቸዋል። 15 ከብቶቻቸውንም አያሳንስባቸውም፤ ከመከራቸውም ሁሉ ከበሽታና ከድካምም፥ ከጥፋትም፥ ከሚያውቁትና ከማያውቁትም ያድናቸዋል። 16 በፍርድም ጊዜ ይከራከርላቸዋል፤ ከክፉ ነገርና ከመከራም፥ ከሚቃወማቸውም ሁሉ ያድናቸዋል፤ በመጀመሪያ የድንኳኑን ሥራ በአደራ የተቀበለ ሌዋዊ የድንኳኑን ሥራ ቢጠብቅ፥ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ቢሄድ፥ በመጀመሪያው ሕግ እንደ ሕጉ ሁሉ ዐሥራቱንና ከሰው ጀምሮ እስከ ከብት ድረስ በኵራቱን ይሰጡት ነበር። 17 ሙሴም የነዌ ልጅ ኢያሱን እንዳዘዘው በሚፈርዱበትና ለሚፈርዱለት ፍርድን እስኪሰጡ ድረስ ባለማወቅ ወይም በማወቅ ነፍስ የገደለ ሰው ቢኖር በዚያ ይድን ዘንድ በከተሞቻቸው ሁሉ መማጸኛ ከተማ ነበር። 18 “ቀድሞ ከእርሱ ጋር ጠብ እንዳለው በልቡናችሁ መርምሩ አላቸው፤ 19 ምሳርም ቢሆን፥ ድንጋይም ቢሆን፥ እንጨትም ቢሆን፥ ባለማወቅ ከእጄ ስለ ወደቀ ያ የወደቀበት ሰው ሞተብኝ ቢል፥ መርምራችሁ አድኑት፤ ባለማወቅ አድርጎታልና ይድናል። 20 በማወቅ ቢያደርገው ግን እንደ በደሉ ፍዳውን ይቀበላል፤ የሚምረውም የለም፤ ባለማወቅ ቢያደርግና ቢገድለው ግን ባለማወቅ አድርጎታልና እንዳይሞት መርምራችሁ አድኑት።” 21 ሙሴም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንዳይተላለፉ ለእስራኤል ልጆች እንደዚህ ሥርዐት ሠርቶላቸው ነበር፤ ከክፋትም ሁሉ እንዲርቁ ሥርዐት ሠርቶላቸው ነበር። 22 በፍርዱና በሕጉ ይኖሩ ዘንድ፥ ጣዖት ከማማለክ፥ ሙቶ ያደረውንና አባላ የተመታውን ከመብላትም፥ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ለሚኖሩና እንደ ሠራላቸው ከክፉ ሥራ ሁሉ ለሚርቁ ለሰው ልጆች ከማይገባው ሁሉ ፈጽመው ይርቁ ዘንድ አዘዛቸው። 23 ነፍሳቸውንም ያድኑ ዘንድ፥ በጎ ከሠሩ ከአባቶቻቸው ጋራ ማደሪያቸውን ያገኙ ዘንድ በሰማይ ባለች ድንኳን አምሳል ከሠራላቸው ትእዛዝ እንዳይወጡ አዘዛቸው። 24 በእግዚአብሔር ቃል ያመኑና በትእዛዙ የሄዱም እነርሱ የጻድቃን ልጆች ይባላሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከአደረጉ ከአዳምና ከሴት ናቸውና። 25 የአዳም ልጆች ነንና፥ በጎ ሥራንና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም ሁሉ እንሠራ ዘንድ በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮናልና አይንቀንም። 26 በጎ ሥራን ብንሠራም በጎ ሥራን ከሠሩ ጋራ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳታለን፤ የሚወዱትን አይለያይምና። 27 በንጹሕ የሚለምኑትን ሰዎች እጅግ ይወዳቸዋል፤ ጸሎታቸውንም ይሰማቸዋል፤ ቈርጠው ንስሓ የሚገቡትንም ንስሓቸውን ይቀበላቸዋል፤ ሕጉንና ሥርዐቱን፥ ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ሰዎች ኀይልንና ጽናትን ይሰጣቸዋል። 28 ፈቃዱንም ያደረጉ ሰዎች ለዘለዓለሙ በመንግሥቱ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል፥ ፊተኞችም ቢሆኑ፥ ኋለኞችም ቢሆኑ ምስጋናን ያቀርቡለታል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም አሜን። |