ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ በፊቱ በቆምን ጊዜ በምድር የሠራነው ሥራችን ሁሉ እንደማይቀርና እንደማይሰወር እመኑኝ። 2 ለመንገዳችንም ስንቅ ባልያዝን ጊዜ፥ ለሰውነታችንም ልብስ በሌለን ጊዜ፥ 3 ለእጃችንም ምርጕዝ፥ ለእግራችንም ጫማ በሌለን ጊዜ፥ 4 ድጥም ቢሆን፥ ጐጣጕጥም ቢሆን፥ ጨለማም ቢሆን፥ እሾህም፥ አሜኬላም ቢሆን፥ የባሕር ጥልቅም ቢሆን፥ የጕድጓድም ጥልቅ ቢሆን እኛን የሚወስዱበትን ጎዳናውን በማናውቅበት ጊዜ። 5 የሚወስዱንንም አናውቃቸውም፤ ነገራቸውንም አንሰማም። 6 እነርሱ ጥቋቍሮች ናቸውና፥ ወደ ጨለማም ይመሩናልና፥ ፊታቸውን አናይም። 7 ነቢዩ ዳዊት እንደ ተናገረ፥ “ነፍሴ በላዬ በአለቀች ጊዜ አቤቱ ጌታዬ ጎዳናዬን አንተ ታውቃለህ፥ በዚች በሔድሁባትም ጎዳና ወጥመድ ሰወሩብኝ፤ ወደ ቀኜም ተመልሼ አየሁ፤ የሚያውቀኝም አጣሁ፤ የማመልጥበትም የለኝም።” 8 ይህንም በተናገረ ጊዜ፦ አጋንንት እንደሚዘባበቱበትና ወደማያውቀው ጎዳና እንደሚመሩት ስለሚያውቅ ነው። ወደ ቀኝና ወደ ግራም ቢመለስ የሚያውቀው ሰው አላገኘም። 9 እርሱንም የሚያውቀው አልነበረም፤ ነገር ግን በጨለማ መላእክት መካከል ነበረ። 10 የጻድቃንን ነፍሳት ይቀበሉ ዘንድ፥ ወደ ሕይወት ብርሃን ቦታም ይወስዱ ዘንድ ወደ ደጋጉ የሚላኩ ረቂቃን መላእክተ ብርሃን ናቸው። 11 ይቀበሏቸው ዘንድ፥ በሠሩት ኀጢአታቸውም ፍዳቸውን ሊቀበሉ ወደ ተዘጋጀላቸው ዘለዓለማዊ ቅጣት ይወስዷቸው ዘንድ ወደ ኃጥኣን ነፍሳት የሚላኩ ግን መላእክተ ጽልመትና አጋንንት ናቸው። 12 ወደ ጥፋት ለሚወስዷቸው ዕረፍትና ድኅነት ካገኛቸውም መከራ እስከ ዘለዓለም ድረስ ማምለጥና መውጣት ለሌላቸው ለኃጥአን ነፍሳት ወዮላቸው። 13 በቃየን መንገድ ሄደዋልና፥ በበለዓምም በደል ዋጋ ጠፍተዋልና፥ የሚያደርጉትንም አጥተዋልና። ገንዘባቸው ያልሆነውን የባዕድ ገንዘብ በግፍ ይወስዱ ዘንድ መማለጃንና አራጣን ለመቀበል ያመካኛሉና። 14 እነርሱም እንደ ሠሩት ሥራቸው በገሃነም እሳት ፍዳቸውን ይቀበላሉ። |