ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ረአይ የሚሉት ነቢይ እንዲህ አለው፥ “በጊዜው ብርሃን ዛሬ ጥቂት ደስ ይበልህ፤ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔርም ባልተጠራጠርኸው መቅሠፍት ይበቀልህ ዘንድ አለው። 2 ፈረሶች ፈጣኖች ናቸው፤ ስለዚህም በሩጫ አመልጣለሁ ትላለህን? 3 እኔስ የሚከተሉህ ሰዎች ከአሞሮች ይፈጥናሉ፤ ከጥፋትና ከሚመጣብህ ከእግዚአብሔር ቍጣ አታመልጥም እልሃለሁ። 4 የብረት ልብስ እለብሳለሁ፤ የጦር መወርወርና የቀስትም መንደፍ አይችለኝም ትላለህን? የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔርም የምበቀልህ በጦር መወርወር አይደለም ይላል፤ ነገር ግን ከጦር መወርወርና ከቀስት ንድፈት የሚከፋ ጽኑ የልብ በሽታን፥ እከክንና ቍርጥማትን አመጣብሃለሁ፤ 5 ቍጣዬን አነሣሥተሃልና፥ የልብ በሽታን አመጣብሃለሁ፤ የሚረዳህም ታጣለህ፤ ስም አጠራርህንም ከምድር እስካጠፋው ድረስ ከእጄ አታመልጥም። 6 አንገትህን አደንድነሃልና ራስህንም በከተማዬ ላይ ከፍ ከፍ አድርገሃልና፥ ይህን ነገር እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥኜ ባደረግሁ ጊዜ እኔ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቀኛለህ፤ አንተ በፊቴ እሳት እንደሚበላው በነፋስ ፊት እንዳለ ሣር ነህና፥ ዓውሎ ነፋስም ከምድር አፍሶ እንደሚበትነው ትቢያ ነህና አንተ በእኔ ዘንድ እንዲሁ ነህ። 7 ቍጣዬን አነሣሥተሃልና፥ ፈጣሪህንም አላወቅህምና እኔም የአንተ የሆነውን ሁሉ ቸል እለዋለሁ፤ በአንባህም ሁሉ ላይ የሚጠጋውን አላስቀርም። 8 አሁንም ከሠራኸው ክፋት ሁሉ ተመለስ፤ ብትመለስ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ፈጽመህ በልቅሶና በኀዘን ብትናዘዝ፥ በንጹሕ ልቡናም ወደ እርሱ ብትለምን በፊቱ የሠራኸውን ኀጢአትህን ሁሉ እግዚአብሔር ይቅር ይልሃል።” 9 የዚያን ጊዜም መቃቢስ ትቢያ ለብሶ ስለ ኀጢአቱ በእግዚአብሔር ፊት አለቀሰ። እግዚአብሔር ተቈጥቶታልና። 10 እግዚአብሔርም በነቢዩ ቃል የተናገረውን መቅሠፍት እንደማያዘገይ ዐወቀ። ዐይኖቹ የተገለጡ ናቸውና አይተኛም፤ ዦሮውም የተከፈተ ነውና ቸል አይልም፤ የተናገረውንም ቃል ሐሰት አያደርግምና በአንዲት ጊዜ እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ ያደርጋታል። 11 ልብሱንም ጥሎ ማቅ ለበሰ፤ በራሱም ላይ ትቢያ ነሰነሰ፤ ስለ ሠራውም ክፋት በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፊት ጮኸ፤ አለቀሰም። |